Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ሁለት ወራት ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች ለመከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 60 ሺህ ዜጎች ደም በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊቱ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን የብሔራዊ ደም ባንከ አገልግሎት ገለጸ።

የብሔራዊ ደም ባንከ አገልግሎት የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ ደም የሚለግሱ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን አስታውቋል።

ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው አሸባሪው ህወሃት ሃገር ለማፍረስ እያከናወነ ያለውን ተግባር በመመከት ረገድ አኩሪ ታሪክ እየጻፉ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።

ዜጎች ለሃገሩ ህልውና እና ለወገኑ ደህንነት ህይወቱን ሳይሰስት እየከፈለ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ አጋርነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው።

ይህም በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የደም ክምችት እጥረት በመቅረፍ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው የመከላከያ እና የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት የሚገልጹት።

የመከላከያ ደም ባንክ ዳይሬክተር ሻምበል ዶክተር ብርሃኑ ካሳዬ እንደሚሉት÷ ኢትዮጵያውያን ለመከላከያ ሠራዊቱ ከሚያደርጉት የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ የደም እጥረት እንዳያጋጥም ደም በመለገስ አበረታች ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

“ደም ህይወት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ዜጎች ደም በመለገስ ረገድ እያሳዩት ያለው ተሳትፎ ለሠራዊቱ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል።

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ በበኩላቸው÷ የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ ጀምሮ የደም ለጋሾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ገልጸዋል።

ባለፉት ሀምሌና ነሃሴ ወራት ብቻ 60 ሺህ ዜጎች ደም በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊቱ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውንም ነው ያነሱት።

ዘመቻውን ተከትሎ ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ በደም ባንኩ ውስጥ የደም ክምችት መጠን መጨመሩንም ተናግረዋል።

በዚህም እንደሃገር የደም የክምችት መጠን ወደ 20 ሺህ ዩኒት ማደጉን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ለሀገሩና ለወገኑ ህይወቱን አሳልፎ እየሰጠ ለሚገኘው ሠራዊት ደም የመለገሱን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.