Fana: At a Speed of Life!

ኮሌጁ አይዘጋም – የመቄት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥትና ኅብረተሰቡ በቁጭት ግብዓቶችን በማሰባሰብ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ይደረጋል እንጂ ኮሌጁ አይዘጋም ሲሉ የመቄት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።

አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ባደረሰበት ውድመትና ዘረፋ ምክንያት ነባርም ሆነ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እንደሚቸገር የመቄት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ገልጿል።

ወራሪው ቡድን ፍላቂት ከተማን በወረረበት ወቅት በርካታ የመንግሥትና የግል ተቋማት ላይ ውድመትና ዘረፋ ፈጽሟል።

ተማሪ ደረጄ ተስፋው በመቄት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሲሆን÷ “ለምዘና ዝግጁ እየሆንን ሳለ ነው አሸባሪው ቡድን ኮሌጃችንን የዘረፈብን እና ያወደመብን” ብሏል።

ለምዘና የተገዛ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ፣ ከ90 በላይ ኮምፒዩተሮች፣ ከ30 በላይ ማሽኖች፣ የድራፍቲንግ ዘመናዊ ወንበሮች፣ ከ400 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የታሸገ ወረቀት እና ሌሎች የኮሌጁ ንብረቶች መዘረፋቸውንና መውደማቸውን የኮሌጁ ምክትል ዲን መልካም አባተ ተናግረዋል።

በዚህም ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት ሲያስተምራቸው የቆየውንና አዲስ ተማሪዎችን በተሟላ መልኩ ለማስተማር እንደሚቸገር ነው ምክትል ዲኑ የጠቆሙት።

የመቄት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ 1 ሺህ 500 ተማሪዎችን እያስተማረ እንደነበረ የተናገሩት አቶ መልካም÷ በዘንድሮ የትምህርት ዘመንም 250 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ እንደነበረም አስረድተዋል።

ኮሌጁ ሥራ እንዲጀምር መንግሥትና ኅብረተሰቡ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኮሌጁ ከውድመት በተረፈው ቁሳቁስና ሌሎች ግብዓቶችን በማሰባሰብም ቢሆን ተማሪዎችን ማስተማር እንደሚቀጥል አቶ መልካም አስገንዝበዋል።

የመቄት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በሪሁን ተረፈ የመቄት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠረ፣ ወጣቶች የተለያየ ሙያን ቀስመው የራሳቸው የሥራ እድል የፈጠሩበት፣ በጥራት ትምህርት በመስጠት እውቅና ያገኘ ኮሌጅ ነው ብለዋል።

“መንግሥትና ኅብረተሰቡ በቁጭት ከየአካባቢው ግብዓቶችን በማሰባሰብ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ይደረጋል እንጂ ኮሌጁ አይዘጋም” ብለዋል።

አቶ በሪሁን መንግሥትና ኅብረተሰቡ በመቀናጀት የተዘረፉና የወደሙ ንብረቶችን በመተካት ኮሌጁ በየደረጃው የመማር ማስተማሩን ሂደት ይቀጥላል ነው ያሉት።

መላው ኢትዮጵያውያን የወደመውን ንብረት ለመተካት ርብርብ እንዲያደርጉ ዋና አስተዳዳሪው መጠየቃቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.