Fana: At a Speed of Life!

በሃገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በሃገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ያልተፈቀዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ መያዙን አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲዉ በ2013 ዓ.ም ብቻ በተለያዩ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ስምንት የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ወደ ሃገር ዉስጥ ሊገቡ ሲሉ ይዟል፡፡

በሃገር ደረጃ ሊያደርስ የነበረዉን ከ19 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኪሳራ ማዳን መቻሉን በኤጀንሲዉ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር ዲቪዥን ኃላፊ አቶ እሸቱ ቡሬሳ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት የደህንነት ስጋታቸዉ ከፍተኛ የሆኑ በ14 ድርጅቶች ስም የመጡ 49 ድሮኖችና የስለላ ካሜራዎች ወደ ሃገር ዉስጥ እንዳይገቡ መከልከላቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ወደ ሃገር ዉስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ከተደረገባቸዉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርቶች መካከልም የቴሌኮም ፍራዉድ መፈጸም የሚያስችል ሲም ቦክስ ፣ ስፓይ ካሜራ፣ ሳተላይት ስልክ፣ ድሮን ፣ የመገናኛ ሬዲዮ፣ ወታደራዊ ባይነኩላር እና የቅኝት መሳሪያዎች፣ ለሰቪላዊና ዎታደራዊ አገልግሎት የሚዉሉ ጂፒኤሶች፣ ድብቅ የድምፅ መቅጃ ማይክራፎኖች፣ ዱዋል ባንድ ራዉተር፣ Transmitters (fm) እና vsat ይገኙበታል ተብሏል፡፡

በመሆኑም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምርት አስመጪዎች ወደ ሃገር ዉስጥ እንዳይገቡ ክልከላ የተደረገባቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ዓይነት በመለየት ማስመጣት እንደሚገባቸዉ ኃላፊዉ ማሳሰባቸውን ከኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.