Fana: At a Speed of Life!

አንድነታችን የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን ጋሬጣዎች የምንሻገርበት ኃያሉ ክንዳችን ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

መልዕክቱም እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ በፈጸመው ወረራ እና በከፈተው ጦርነት ማሸነፍ እንደማይችል አሳምሮ ይገነዘባል፡፡

በለኮሰው ጦርነት እንኳንስ ማሸነፍ ቀርቶ በህይወት መትረፍ እንኳን እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡

የትህነግ ዓላማ በጦርነቱ ምክንያት ድኅነት እና ጉስቁልናን በማባባስ አማራን አዳክሞ፤ የብሔር ብሔረሰቦችንም አንድነት አጥፍተው ኢትዮጵያ በውጭና በውስጥ ባንዳዎች በጠላቶቿ የተቀነባበረባትን ሁለንተናዊ ጥቃት መመከት የማትችል ደካማ ሃገር ለማድረግ ነው፡፡

ለዚህም ነው በቢሊየን ብር ወጪ ተደርጎባቸው የተገነቡ የመሰረተ ልማት ውጤቶችን አፍርሰው ካወደሙ በኋላ እንደገና መብራት ይሰራልን፤ ስልክ ይቀጠልልን፤ ድልድይ ይገንባልን የሚል እንቶፈንቷቸውን የሚነዙት፡፡

አንዳንድ የትህነግ አይዞህ ባይ ዓለም አቀፍ የእርዳታና የሚዲያ ተቋማት ጭምር ትህነግ የፈጸማቸውን የመሰረተ ልማት ውድመቶች ሳይቃወሙ፤ የወደሙ የመሰረተ ልማቶች በአስቸኳይ እንዲገነቡ ሲሉ መደመጣቸው መንግሥትን የበለጠ ደሃ በማድረግ የምጣኔ ሃብት ጫና ለመፍጠር የሚችሉበትን እድል ለማመቻቸት እየተውተረተሩ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ ግብዓቶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የሄዱ 428 ተሽከርካሪዎችን አግቶ ያስቀረውን ትህነግን ሳያወግዙ መንግሥት ተጨማሪ የእርዳታ ግብዓቶችን እና ነዳጅ ወደ ትግራይ እየላከ አይደለም የሚል ክስ ለመንዛት መሯሯጣቸው መንግሥትን ከማዳከም ጎን ለጎን በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን አሸባሪውን ለመታደግ የሚያደርጉትን ዐይን ያወጣ ውንብድና ይመሰክራል፡፡

ይህን በደል ከስር መሠረቱ የተገነዘበው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸባሪው ትህነግ ጦርነት በከፈተባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል ሕዝብ ጎን ተሰልፈው ትህነግን ከመዋጋት ባሻገር÷ በገንዘብ፣ በምግብ አቅርቦት እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረባቸውን ሁለንተናዊ ጫና በመጋራት የትህነግን እና የአይዞህ ባዮቹን ወጥመድ እየበጣጠሱት ይገኛሉ፡፡

ለአብነትም በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ወረራውን ለመቀልበስ በአማራ ክልል ለሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ሕዝባችን ያደረገውንና እያደረገ ያለውን ድጋፍ መጥቀስ ይቻላል፡፡

መላዉ ኢትዮጵያዊያን ለአብነትም የሲዳማ ክልል ሕዝብ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እና አንዳንድ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ከአማራ ሕዝብ ጎን ሆነው ያደረጉት በሺዎች የሚቆጠሩ የቁም እንስሳትን፣ የቁሳቁስ እና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ከቁሳዊ ድጋፍነቱ የበለጠ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ያጸና ህያው ተግባር ሆኖ በታሪክ ሲጠቀስ ይኖራል፡፡

ትህነግ እና ታሪካዊ የውጭ ጠላቶቻችን በጦርነትና ጦርነት በሚወለደው ድኅነት ሊበትኑን ቢከጅሉም ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ግን የከፈቱብንን ጦርነትም ሆነ የቀበሩትን የድህነት ፈንጅ እየመነጠርን ለማምከን አስችሎናል፡፡

አሁን በተግባር እየጎለበተ የሚታየው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን አጠናክረን ልናስቀጥል ይገባል፡፡ ምክንያቱም የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን ጋሬጣዎች የምንሻገርበት ኃያሉ ክንዳችን እሱው ነውና፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.