Fana: At a Speed of Life!

በማይጠብሪ ግንባር ለ25 ቀናት ሁለት የቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ደብቀው ከጁንታው የታደጉት አርሶ አደር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤተሰባቸውን ህይወት አደጋ ላይ ጥለው ለ25 ቀናት ሁለት ጉዳት የደረሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከብሬን ጦር መሳሪያ ጋር ደብቀው ከጁንታው የታደጉት አርሶ አደር ቤተሰቦች ደጀንነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል።
አርሶ አደር ክብረት ጸሃይነህ ይባላሉ።በሰሜን ጎንደር ዞን አዲ ዓርቃይ ወረዳ ልዩ ስሙ አምበር በተባለ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።
የሽብር ቡድኑ ህወሓት ባሳለፍነው ነሐሴ ወር መጀመሪያ ቀናት ላይ በአካባቢው ሰርጎ በመግባት የአድርቃይ ወረዳን ለመያዝ ችሏል።
በዚህ ወቅት በነበረው ውጊያም የብሬን ጦር መሳሪያ ተኳሽ የሆኑት አስር አለቃ ነስሩ መሃመድ እና ወታደር እያሱ ሰለሞን ከጠላት ጦር ጋር ሲፋለሙ ጉዳት ይደርስባቸዋል።
ይህን ተከትሎም አስር አለቃ ነስሩ እራሱን ከጁንታው ለማትረፍ የተለያዩ ወታደራዊ ስልቶችን ተጠቅሟል።
ከአንድ አሰቃቂ ሌሊት ቆይታ በኋላም አስር አለቃ በአቅራቢያ የአንድ አርሶ አደር ቤት ይመለከታል።
ቆስሎ ስለነበር ቀስ ብሉ እየዳኽ አርሶ አደሩ ቤት ከደረሰ በኋላም እርዳት ይጠይቃቸዋል።
የወገን ጦር መሆኑን የተረዱት አርሶ አደር ክብረት ጸሃይነህም ምንም ሳያቅማሙ በፍጥነት ወደ ቤት አስገቡት።
አረሶ አደሩ በወቅቱ የወገን ጦር የደረሰበትን ጉዳት እና ሁኔታ ሳየው ‘አንጀቴ ተንሰፈሰፈ’ ሲሉ የተሰማቸውን የተዘበራረቀ ስሜት ያስታውሳሉ ።
አይዙህ የቆሰልከው በተጣለብህ ሃላፊነት መሠረት መስዋዕት ሆነህ እኛን ከሽብር ቡድኑ ልትጠብቅ ብሎም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ስትፋለም ነው፤እናም ለዚህ ውለታህ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንከፍላለን፤ አንተም እኛ የሆነውን ትሆናለህ ምንም አትጨነቅ በማለት እንዳጽናኑትም ይናገራሉ።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ይርገዱ መርሻም አስር አለቃ ነስሩን በደስታ ተቀብለው ቆስሎ የገረጣ ሰውነቱን ለመጠገን ቤት ያፈራውን በመስጠት የእናትነት ፍቅራቸውን አሳዩት፤ መንከባከብም ጀመሩ።
ጉዳት የደረሰበት አካሉ እንዲያገግም ቁስሉን በጨው ዘፍዝፈው ከማጠብ ጀምሮ በባህላዊ መንገድ አስፈላጊውን ህክምና አደረጉለት።
አይዞህ አኔም አንተን የሚመስሉ ልጆች አሉኝ፤ ነገ ምን እንደሚገጥማቸው አላውቅም፤ ፈጣሪ ሊያተርፍህ እዚህ ቤት አምጥቶሃል ፤ ለእሱ የሚሳነው ነገር የለምና አትስጋ በማለት እንዳበረታቱት ይናገራሉ።
አስር አለቃ ነስሩ ግን አርሶ አደሮቹ በህወሓት ቁጥጥር ስር ሆነው እንኳ ለማያውቁት አንድ ወታደር እያሳዩት ያለው ወገናዊነትና እንክብካቤ በሲቃ አስለቀሰኝ ሲል ያን የጭንቅ ቀን ያስታውሳል።
ይህ ሀሉ ሲሆን የጠላት ጦር አካባቢውን ተቆጣጥሮ በቀጣይ ደባርቅን ለመያዝ ከወገን ጦር ጋር ከባድ ፍልሚያ እያደረገ ነው።
ከከባድ መሳሪያ እስከ ቀላል መሳሪያ ይተኮሳል፤ የጦር መሳሪያ ድምጽ በአካባቢው ያጓራል፤ የሰፈሩን ሰውም አስጨንቆታል፤ ሁሉም እራሱን ከጥቃቱ ለማዳን ይሸበራል፤ አምበር ቀበሌም የጦር ቀጠና ሆናለች።
ጅንታው የንጹሐን ቤት እየገባ እያስገደደ ከመዝረፍ ጀምሮ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱን ተያይዞታል።
አሁን የእነ አርሶ አደር ክብረት ቤተሰብ ከሰፈር ነዋሪዎች በተለየ መልኩ ለተጨማሪ ችግር ተዳርጓል።
የመጀመሪያው እራሳቸውን ከጁንታው ጥቃት መከላከል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የቆሰለውን የመከላከያ አባል በመደበቅ ከህወሓት አረመኔያዊ ጥቃት መታደግ።
የሽብር ቡድኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን እንደደበቁ መረጃ ከደረሰውም በቤተሰቡ ላይ ሊወሰድ የሚችለውን እርምጃ ማሰብና መወሰንም ሌለኛው ከባድ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ውሳኔ ነበር።
ከዚህ ሁሉ ጭንቀት በድል ለመውጣትም ቤተሰቡ አንድ መላ ዘየደ።
አካባቢውን የተቆጣጠረው የጠላት ጦር ድንገት ቢመጣ አስር አለቃን እንዳያገኘው ቀን ጫካ ውስጥ አሳቻ ቦታ መደበቅ እና ማታ ደግሞ ቤት አምጥቶ ማሳደር።
መረጃ ሊጠቁሙ የሚችሉ የመከላከያ ደንብ ልብሱን እና ብሬን የተሰኘውን የጦር መሳሪያም ከቤት አርቀው ደበቁ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከአንድ ቀን ቆይታ በኋላ በተመሳሳይ ጊዜ በጠላት ቆስሎ የነበረው የአስር አለቃ ነስሩ ጓድ ወታደር እያሱ ሰለሞን ወደ ቤት መጥቶ ደጀን እንዲሆኑት ይጠይቃል።
አቶ ክብረትም ቤት የእግዚአብሄር ነው በማለት ወደ ቤታቸው ያስገቡታል።
ሁለቱ የወገን ጦር አባላት ከሞት አፋፍ ተርፈው አንድ ላይ ሲገናኙ የተሰማቸውን የደስታ ስሜት እና ሲቃ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል ይላሉ አርሶ አደር ክብረት፤እሳቸውም በደስታ አብረዋቸው እንዳለቀሱ ያስታውሳሉ።
ከዛን ቀን ጀምሮም ይህ ቤተሰብ ንጋት ላይ ማንም ሳያይ ሁለቱን ወታደሮች ጫካ ወስዶ አሳቻ ቦታ ውስጥ ይደብቃል፤ ማታ ላይ ጭር ሲልም ቤት አምጥቶ በሥርዓት ተንከባክቦ ያስተኛል።
የዚህ ደግ እና ጀግና ቤተሰብ ተግባርም ለ25 ተከታታይ ቀናት በከፍተኛ ጥንቃቄ ቀጥሏል።
በዚህ ሒደት ላይም አርሶ አደር ክብረት አስጨናቂና አስፈሪ ጊዜ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።
ከጭንቀታቸው የተነሳም ወታደሮቹ እና ቤተሰቦቻቸው ሳያዩ ፈጣሪያቸውን አልቅሰው ለምነዋል፤ እግዚአብሄር ሆይ የእነዚህ ወታደሮች የህይወት እጣ ፈንታ እኔ ላይ ጥለኸዋልና የቤተሰቤንም ሆነ የእነሱን ህይወት አንተው ጠብቅልኝ? ብለው ወደ ፈጣሪ ማልቀሳቸውን ያስታውሳሉ።
የጠላት ጦር መረጃ እንዳይደርሰው ጉዳዩን በጥብቅ ምስጢር ከመያዝ ባለፈም እንቅስቃሴውን በንቃት ሲከታተሉ መቆታቸውንም በቤታቸው ለተገኘው የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጋዜጠኞች ቡድን አስረድተዋል።
ወታደሮቹ ቀን አብረው ሲውሉ በስህተት እንዳያወሩና እና ድምጽ እንዳያሰሙም የተለያየ ቦታ ላይ እንዲደበቁ አድርገዋል።
የ12 ክፍል ተማሪ የሆነው ልጃቸው መከታው ክብረትም ከስነ ዜጋ ትምህር በቀሰምኩት ዕውቀት መሠረት መከላከያ የሀገር አለኝታ እና መከታ ነው፤የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርም ኑሮው በቀበሮ ጉድጓድ የተወሰነ ነው።እናም እኔን ለማዳን የመጣን የወገን ጦር አስፈላጊውን ሁሉ ሳደርግ ቆይቻለሁ በማለት ይናገራል ።
በተይም ሊነጋ ሲል በአካባቢው የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ካጤነ በኋላ ቁስለኞችን አዝሎ የሚደበቁበት ቦታ መውሰዱ የዕለት ተዕለት ተግባሩ እንደነበር አጫውቶናል።
ከ25 የጭንቅ ቀናት በኋላም የወገን ጦር አካባቢው ላይ በነበረው የህወሓት ሽብር ቡድን ላይ በፈጸመው ከባድ ምት ጁንታው ስፋራውን ለቆ ፈርጥጧል።
አካባቢው የሰላም አየር መተንፈሱን ተከትሎም አቶ ክብረት ለ25 ቀናት የቤተሰባቸውን ህይወት አደጋ ላይ ጥለው ደብቀው ሲንከባከቧቸው የቆዩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እና ብሬን የተሰኘውን የጦር መሳሪያ በማይጠብሪ ግንባር ለሚገኙት ከፍተኛ የጦር መሪዎች ማስረከባቸውን ነግረውናል።
አስር አለቃ ነስሩ እና ወታደር እያሱ በቆይታቸው ወቅት የአርሶ አደር ክብረት ቤተሰብ ያደረገላቸው እንክብካቤ ከህሊና በላይ መሆኑን ይናገራሉ።
“ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ፣ሰው የጠፋ ዕለት” ሲሉም የአርሶ አደሩን ቤተሰብ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል በጎ ተግባር በምሳሌ አስረድተዋል።
እንደዚህ እይነት አስተማማኝ ደጀን ለሚሆን ህዝብ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመከፈል ዝገጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በመላኩ ገድፍ
(ማይጠብሪ ግንባር)
+2
109,510
People Reached
18,195
Engagements
Boost Post
5.9K
219 Comments
463 Shares
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.