Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ ከተለያዩ ሀገራት አቻዎቻቸውና ከተቋማት አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት አረብ ኤመሬትስ፣ ከጋቦንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርሮችና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ጋር በኒውዮርክ ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በ76ተኛ የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ አሜሪካ የሚገኙት አቶ ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአመራሮቹ ጋር በኒውዮርክ ተገናኝተው ነው በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በሰፊው የተወያዩት።
ከጋቦን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓኮሜ ሞቤሌት ቡቤያ ጋር አቶ ደመቀ ባካሄዱት ውይይት፥ ጋቦን በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቀጣይ አባል መሆኗን ተከትሎ÷ ለአፍሪካውያን ድምፅ በመሆን ሚናዋን እንደምትወጣ እምነታቸውን ገልፀዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ቀንድ ያለው ትኩረት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ÷ አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሄ እንዲያገኙ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል።
በተመሣሣይ አቶ ደመቀ መኮንን ከቬንዙዌላ የውጭ ግንኙነት ሚኒስትር ፌሊክስ ራሞን ፕላስሴሲያ ጎንዛሌዝ ጋር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በቀጣይ በሃገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና የትብብር ማዕቀፍ ለማስፋት ትርጉም ያላቸው ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ባስሌይ ጋር እንዲሁ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት÷ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል መንግሥት በሃላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት መሬት ላይ ያለ እውነት በመሆኑ ሊሸፈን እንደማይገባው በአፅንኦት ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብዓዊ ስጋቶችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን÷ በተደጋጋሚ የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የሚገጥሙ ችግሮችን አብራርተዋል።
በሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር መንግሥት በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመጠቆም÷ በቀጣይም ውጤታማ በሆነ አግባብ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥን በማመቻቸት ረገድ በመንግስት ላይ ሚዛናቸውን ያልጠበቁ እና ትክክለኛ ያልሆኑ ክሶች ተደጋግመው እንደሚነሱ አውስተው÷ በመንግስት በኩል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በችግሩ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች በሙሉ ተደራሽ ያደረገ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.