Fana: At a Speed of Life!

የአይሳይታ-አፋምቦ- ጅቡቲ ድንበር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ጥር 27፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የአይሳይታ-አፋምቦ- ጅቡቲ ድንበር የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የአስፋልት መንገድ ግንባታው መንግስት በመደበው 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የተጀመረ ሲሆን፥ በሶስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ 48 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፥ የመንገዱ ደረጃ ማደጉ ለሀገሪቱ አማራጭ የወጪና ገቢ ንግድ መስመር ሆኖ እንዲያገለግል የታሰበ መሆኑን የባልስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽንና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልጸዋል፡፡

ግንባታውን አሰር ኮንስትራክሽን የተሰኘ ሀገር በቀል ስራ ተቋራጭ የሚያከናውነው ሲሆን፥ ይዲዲያ ኢንጂነሪንግ ድርጅት ደግሞ በአማካሪነት ይሳተፋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አይናለም ፍቃዱ፥ አሁን ላይ ከካምፕ ስራ በተጓዳኝ 23 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የመንገድ አካል የሚሸፍን የመሬት ቆረጣና ሙሌት ስራ እየተካሔደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመንገድ ስራ ተቋራጩ 400 ለሚሆኑ የአካባቢው አርብቶ አደር ልጆች በተለያየ የሙያ መስክ የስራ እድል መፍጠሩንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የአፋምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ዓሊ በበኩላቸው፥ መንገዱ ሲጠናቀቅ ከፊል አርብቶ አደሮች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ በማቅረብ በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የአቢ ሃይቅን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር መንገዱ ገንቢ ሚና ይጫወታል የሚል ተስፋ ማሳደሩን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.