Fana: At a Speed of Life!

በስምምነቱ የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት በዘላቂነት በማያስጠብቅ ሁኔታ አንድም ቃል ከተካተተ አንፈርምም- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን በወንዙ የመጠቀም መብት በዘላቂነት በማያስጠብቅ ሁኔታ አንድም ቃል ከተካተተ ኢትዮጵያ እንደማትፈርም የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር የሀገራችንን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

ግድቡን በተመለከተ አሜሪካና የአለም ባንክ በታዘቢነት በተገኙበት በአራት የተለያዩ ዶክመንቶች ላይ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ድርድር አካሂደው ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በዋናነት የግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በሚመለከት ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ በተለይም ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የሦስቱን ሀገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተካሂዷል ብለዋል።

በቴክኒካዊ፣ በህጋዊ፣ በግጭት አፈታት እና በትብብር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በአጭር ጊዜ መፈራረም እንችላለን ብለዋል።

አያይዘውም ወደፊትም የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት በዘላቂነት በማያስጠብቅ ሁኔታ አንድም ቃል ከተካተተ ኢትዮጵያ እንደማትፈርም ሚኒስትሩ በአጽንኦት ገልጸዋል።

የህግ አማካሪዎቻችን የካበተ ልምድ ያላቸው ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፥  የኢትዮጵያ ጥቅም ተላልፎ እንደተሰጠ በማስመሰል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚናፈሰው ወሬ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.