Fana: At a Speed of Life!

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አንዳንድ የአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና በረራ ማቋረጣቸው ተቀባይነት የለውም – የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸው ተቀባይነት እንደሌለው የአፍሪካ ህብረት የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ገለፀ።

የማዕከሉ ዳይሬክተር ጆን ንኬንጋሶንግ፥ እስካሁን በአፍሪካ በቫይረሱ የተጠቃ አንድም ሰው አለመኖሩን አረጋገጠዋል።

ይሁን እንጅ በሁሉም የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ቫይረሱ ወደ ሀገራቸው እንዳይገባና ምናልባት ቢገባ በምን መልኩ መቆጣጠር እንደሚገባ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም ወደ ቻይና ቀጥታ በረራ ያላቸው አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት በረራ ማቆማቸውን ጠቅሰው፥ ይህ ተቀባይነት እንደሌለው እና ትክክለኛው መንገድ ጥንቃቄ ማድረግ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በዚህ ጉዳይ ላይ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን ‘በረራ መቆም የለበትም’ የሚለውን አቋም በተመሳሳይ እንደሚከተል ነው ያረጋገጡት።

ስለዚህም ወደ ቻይና በረራ የሚያደርጉ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሀገራት ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በአህጉር ደረጃ ሁሉን አቀፍ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

“አምስት ተግባራትን በአፍሪካ ደረጃ እያከናወንን ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የመጀመሪያው የላቦራቶሪ ምርመራን በተመለከተ ፈጣን የአቅም ግንባታ ሥልጠና በሴኔጋል እየተሰጠ” መሆኑን አስረድተዋል።

ማዕከሉ በመጀመሪያ ደረጃ ከሚያከናውነው የሥልጠና መርኃ ግብር ውስጥ በአንደኛው ዙር ከ15 ሀገራት የተውጣጡ 15 የጤና ባለሙያዎች በቤተ ሙከራ ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሁለተኛ ዙር ደግሞ 20 የጤና ባለሙያዎች ከ20 ሀገራት እንደሚሳተፉ ጠቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሁሉም የአፍሪካ አባል ሃገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች ሥልጠናውን ይወስዳሉ ብለዋል።

በቅርቡ ደግሞ በአውሮፕላን ማረፊያዎች አካባቢ የሚደረገውን የምርመራ ሥራ በጥራትና ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን እንዲተገበር ለማስቻል የሚያግዝ ሥልጠና እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ሥልጠናዎቹ የኮሮና ቫይረስ ወደ አፍሪካ እንዳይገባና ከገባም በተሳካ መልኩ ሕክምና በመስጠት የቫይረሱን ሥርጭት በጊዜ ለመቆጣጠር ይረዳልም ነው ያሉት።

ያም ሆኖ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ፈጣን መሆኑን አንስተው አፍሪካውያን ቫይረሱን በቀላሉ ለመከላከል የግል ንጽህናን መጠበቅ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.