Fana: At a Speed of Life!

ከቻይና ውሃን ከተማ የሚመጡ ሁሉም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲገቡ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከቻይና ውሃን ከተማ የሚመጡ ሁሉም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲገቡ መወሰኑን መደረጉን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ።

ኢንስቲቲዩት የኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ ሁኔታ እና በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በመግለጫው፥ የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ እስከ አሁን ድረስ 29 ጥቆማዎች በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ ለሚገኘው የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰዋል ብለዋል።

29ኙ ላይ በተደረገው ማጣራት፣ 14ቱ በቫይረሱ የመያዝ ምልክት ያሳዩ ስለነበረ፣ ተለይተው ወደ መቆያ ስፍራ እንዲገቡ ተደርገዋል፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ 11 ናሙናዎች ተልከው ስምንቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፥ 3 ናሙና ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የምርምራው ውጤት እየተጠበቀ ሲሆን በቀጣዬቹ ቀናት 3 ናሙናዎች ለምርመራ የሚላኩ ይሆናል ብለዋል።

በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ተጠርጥረው ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተላኩት ውስጥም አምስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ አንዱ ቻይናዊ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ተጠርጥረው ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተላኩት ውስጥም አምስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ አንዱ ቻይናዊ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽሽን ቀድሞ ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስታወቁት።

ዳይሬክተሩ አክለውም ከቻይና ውሃን ከተማ የሚመጡ ማናቸውም መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲገቡ መወሰኑን ጠቅሰው፥ ወደ ሀገር ውስጥ እንደገቡ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው አስፈላጊው የህክምና ክትትል ይደረግላቸዋል ብለዋል።

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ከሌላው መንገደኛ ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት ምርመራ የሚደረግላቸው ሲሆን፥ በተጨማሪም ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የኢሚግሬሽን ልዩ መስኮት እንደተዘጋጀም ገልፀዋል።

ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን የጤና ሁኔታ መከታተል እንዲቻል ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ አገልግሎት መጀመሩንም አስታውቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ምርመራን በሀገር ውስጥ ለማስጀመር የሚረዱ የመመርመሪያ ቁሳቁሶችም ከውጭ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ መሳሪያዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ እንደገቡ ምርመራው ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ይጀመራልም ነው ያሉት።

የኮሮና ቫይረስ በ25 ሀገራት ላይ የተከሰተ ቢሆንም በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ብቻ እስካሁን የቫይረሱ ተጠቂ አልተገኘም።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.