Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፀጥታ የጋራ ግብረ ሀይል የአሸባሪዎቹን ሸኔና ህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 9፤2014 (ኤፍ ቢሲ) የኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ የጋራ የፀጥታ ግብረ ሀይል የአሸባሪዎቹን የሸኔና የህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን በጋራ እየሰሩ መሆኑን አስታወቁ።

የየክልሎቹ ፖሊስ ኮሚሽነሮች እንዳመለከቱት፤ ከአሸባሪው ህወሃት ጋር በመናበብ በህዝብ ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን አሸባሪው ሸኔ የሚፈጽመውን ድርጊት ለማስቆም የክልሎቹ የጋራ የፀጥታ ግብረ ሀይል ህዝብን ያሳተፈ ዘመቻ እያደረገ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዱልአዚዝ መሀመድ ÷አሸባሪው ሸኔ በህዝብ ህይወትና ንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመከላከል ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በጥምረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ነዋሪዎችን ሰላም እየነሳ የሚገኘውን የሸኔ የሽብር ቡድን በዘላቂነት ለመደምሰስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

አሸባሪው ሸኔ ተሽከርካሪዎችን በማስቆምና ንፁሀንን በማገት ሽብር እየፈፀመ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የፈፀማቸውን ጥፋቶች በመከታተል የጉዳቱን ሰለባዎች ለመታደግ በጋራ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው÷ የህዝብን ሰላምና የአካባቢን ጸጥታ የሚያውከውን የአሸባሪው ሸኔ ቡድን ጥቃት ለማስቆም የክትትል ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮዽያን ለማፍረስ ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር በቀጥታ የጥፋት ተላላኪነት ተግባሩን እየፈፀመ መሆኑን ቡድኑ በፈፀማቸው ወረራዎችና በንፁሃን ላይ ባደረሳቸው ጭፍጨፋና ግድያዎች እያረጋገጠ እንደሆነ ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.