Fana: At a Speed of Life!

ቴሌግራፍ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ላይ ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨቱን እንዲያቆም ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቴሌግራፍ የተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጨውን ሀሰተኛ መረጃ አጠናክሮ የቀጠለበት መሆኑንና ከዚህ ድርጊቱ ተቆጥቦ ትክክለኛ መረጃዎችን እንዲያቀርብ ተጠየቀ፡፡
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚወጡትን ሀሰተኛና የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያጋልጠው የመረጃ ማጣሪያ “ፋክት ቼክ ኢትዮጵያ” ለዘገባው በሰጠው ምላሽ እንዳሰፈረው÷ ቴሌግራፍ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ላይ ሀሰተኛ መረጃዎችን የማሰራጨት ጥረቱን ሆን ብሎ ቀጥሎበታል ብሏል፡፡
ጋዜጣው ” የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ የእርዳታ እህል ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እናደርጋለን ሲሉ ዛቱ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሁፍ ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያላሉትን ነገር በማጣመም ታስቦበትና ሆነ ተብሎ የተዘጋጀውን ሀሰተኛ ጽሁፍ ማውጣቱን አጋልጧል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን ገጽታና አቋም ለማጠልሸት ሆነ ተብሎ የሚካሄድ የምዕራባውያን ሚዲያዎች የሴራ አካል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምግብ እህል ራስን ስለመቻል በቅርቡ ያደረጉት ንግግር፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ በግብርና ምርት ራሷን በመቻልና ስንዴን በብቃት በማምረት ከስንዴ ልመና መውጣት እንዳለባት ያላቸውን እምነት የገለፁበት እንጂ÷ ከውጭ የሚመጣንና ለዜጎቻችን የሚደርስን ሰብዓዊ እርዳታ እናቆማለን እንዳላሉም የመረጃ ማጣሪያው አስገንዝቧል፡፡
ይህንን ትክክለኛ ገለጻ በማጣመም ነው የእንግሊዙ ጋዜጣ ቴሌግራፍ በጽሁፉ ሰብዓዊ እርዳታን ለሚሹ ወገኖቻችን ድጋፍ እንዳይደርስ ፍላጎት እንዳለ አስመስሎ በሀሰት የዘገበው፡፡
ጋዜጣው ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጨው መረጃ አስቀድሞ የተያዘንና የታሰበበትን አጀንዳ ለማስፈጸም የሚረዱትን ዘገባዎች ከማስተናገድ ታቅቦ፥ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር የሚጠይቀውን ደረጃ በመጠበቅ የራሱን ፍላጎት ሳይሆን አንባቢዎች የሚፈልጉትን ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ እንዳለበትም የኢትዮጵያ የመረጃ ማጣሪያ አሳስቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.