Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ወጣቶች ሽብርተኛው ህወሓት የሚያሰራጨውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳና ጥቃትት ለመመከት ዝግጁ ነን አሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአፋር ክልል ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በመመከት ላይ እና በሌሎች የክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሰመራ ከተማ ተካሄደ።
ውይይቱ የሽብር ቡድኑ ህወሓት አሁን ላይ በአፋር ክልል ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመመከት ወጣቶች ማከናወን በሚጠበቅባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች የሽብር ቡድኑ ህወሓት የሚያሰራጨውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለመመከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹ አክለውም የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋትና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት በተባበረ ክንድ በአጭር ጊዜ ማስቆም እንደሚገባና ለዚህም ያላቸውን ዝግጁነት ገለጸዋለ።
አሸባሪ ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ መግደል፤ አፍኖ ማሰቃየትና ዝርፊያ መፈጸም የዕለት ተዕለት ተግባሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
አሸባሪ ሕወሃት ከምስረታው ጀምሮ የአፋር ህዝብ በሰላም እንዳይኖር ያደረገ የግፈኞች ስብስብ መሆኑን የተናገሩት ወጣቶቹ፥ አሁንም ቢሆን የአፋር ህዝብ ፣ ሕጻናት ፣ ሴቶች እና አዛውንት በከባድ መሳሪያ እየጨፈጨፈ መሆኑ እጅግ ያስቆጣቸውና ሊመከቱት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል።
ወጣቶቹ በመጨረሻም እንደ ክልል የቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል፥ አሸባሪው ቡድን ንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመቃወም የህይወት መሰዋእትነት ለመክፈል ጭምር ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
የአፋር ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሴ አዳም በበኩላቸው ÷ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በአደረገበት አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ በከባድ መሳሪያ ግፍ እየፈጸመ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
አሸባሪ ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ሰለማዊ ዜጎችን በጅምላ በመግደል፣ የአርብቶ አደሩ ህልውና የሆኑ የቤት እንስሳትን በመጨፍጨፍ እና ንብረት በማውደም አገር በማፍረስ እኩይ ተግባሩ ቀጥሏል ብለዋል ፡፡
የተለያዩ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫና ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ እንዲያከሽፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሊ ሹምባህሪ
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.