Fana: At a Speed of Life!

የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋትና ኢ-ሰብዓዊ ተግባር በተባበረ ክንድ በአጭር ጊዜ ማስቆም ይገባል-ዶ/ር አረጋዊ በርሄ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሸባሪው ህወሓትን የጥፋትና ኢ- ሰብዓዊ ተግባር በተባበረ ክንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቆም አለብን” ሲል የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ፡፡
 
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንዳሉት÷አሸባሪው ህወሓት የትግራይ ህዝብን ጨምሮ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል፡፡
 
አሸባሪ ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ መግደል፤ አፍኖ ማሰቃየትና ዝርፊያ መፈጸም የዕለት ተዕለት ተግባሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
 
አሸባሪ ሕወሃት ከምስረታው ጀምሮ የትግራይ ህዝብ በሰላም እንዳይኖር ያደረገ የግፈኞች ስብስብ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር አረጋዊ÷ አሁንም ቢሆን የትግራይ ህዝብንና ሕጻናት አስገድዶ በጦርነት እየማገደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
 
ይህ አልበቃ ብሎት በተለየ መልኩ ህጻናትን በጦርነት ውስጥ ከፊት በማሰለፍ ለሰው ልጆች ደንታ የሌለው ስብስብ መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን ገልጸዋል።
 
ባለፉት ጊዜያት በወረራ በያዛቸው የአማራና አፋር ክልሎች አካባቢዎችም ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት በመፈጸም ለሰው ልጆች ጠላትነቱን በተግባር አረጋግጧል።
 
ሰሞኑን እንኳን በደቡብ ወሎ አምባሰልና ውጫሌ እንዲሁም በአፋር ጭፍራ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት የጥፋት ተግባር ፈጽሟል።
 
በተለይ ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ከፊት በማሰለፍ ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው ይታወቃል።
 
ሰሞኑን በፈጸመው ጥቃት ከ20 እና 30 ኪሎ ሜትር ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ የከተማውን ነዋሪ ተሸብሮ እንዲፈናቀል ማድረጉና ከ30 የማያንሱ ንጹሓን ዜጎችን መግደሉን መንግስት መግለጹ ይታወሳል።
 
ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችን በወረራ በመያዝ በርካታ ንጹሃንንና የሃይማኖት አባቶችን ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ከብቶች በጥይት ደብድቦ ጨፍጭፏል፣ ንብረት አውድሟል።
 
የተለያዩ ተቋማትን ንብረቶች በመዝረፍና በማውደም በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ባዶ የሚያስቀር ዘራፊ ቡድንም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።
 
አሸባሪው ህወሃት በተከታታይ በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ህዝብ ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ከመሆኑም በላይ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የእርዳታ እህል እንዳይደርስ በማድረግ ኢሰብዓዊ ተግባር ይፈጽማል።
 
የትዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ እንደገለጹት÷ አሸባሪ ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ሰለማዊ ዜጎችን በጅምላ በመግደል፣ የአርሶ አደሩ ህልውና የሆኑ የቤት እንስሳትን በመጨፍጨፍ እና ንብረት በማውደም አገር የማፍረስ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
 
በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ካሉ ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ጋር ህብረት በመፍጠርና በተናበበ መልኩ ሰለማዊ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ በመፈጸም ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዳይኖራቸው እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
 
የተለያዩ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫና ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ እንዲያከሽፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ህልውና መጠበቅ እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አክለዋል።
 
አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት በሁሉም ጥግ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ሲያሰቃይ መቆየቱን አስታውሰው÷ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ከስልጣን እንዳስወገዱት ተናግረዋል፡፡
 
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሆን “በአገር ህልውና ላይ አደጋ የደቀነውን የአሸባሪው ህወሃት ቡድንን መመከት አለባቸው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ዜጎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት ህዝብን በማስተባበር የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተግባር በአጭር ጊዜ ማስቆም እንዳለበት ተናግረዋል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.