Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ተግባር ለመፈጸምና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በድብቅ ለማስተላለፍ ሞክረዋል የተባሉ የሸኔ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ተግባር ለመፈጸምና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በድብቅ ለማስተላለፍ የሞከሩ የሸኔ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ።
 
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ሽብርተኛው ሸኔ በንፁሃን ዜጎችና በፀጥታ አካላት ላይ ግድያ እንዲፈፅሙ መልምሎና ስልጠና ሰጥቶ ለጥፋት ተልዕኮ ካሰማራቸው ግለሰቦች መካከል በስሩ አምስት የገዳይ ቡድን አባላትን በማደራጀት በህቡዕ ሲንቀሳቀሰ የነበረው ጃፋር መሃመድ ሳኒ የተባለው ተጠርጣሪ በተደረገበት ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
 
ይህ የሸኔ ታጣቂ በቁጥጥር ስር የዋለው በስሩ ካደራጃቸው 5 ግብረ አበሮቹ ጋር በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ኦዳ ቡልቱም ወረዳ ሚደግዱ ቀበሌ እና ቦረማ ጫካ እንዲሁም ዳሮ ለቡ ወረዳ ሚጨታ እና በዴሳ ከተማ ውስጥ በንፁሃን ዜጎች እና በመንግስት ፀጥታ አካላት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በህቡዕ ሲንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል።
 
የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት የተጠርጣሪውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የተቀናጀ ክትትል በማድረግ አቅዶት የነበረውን የሽብር ጥቃት ሳይፈፅም ለጥፋት ተልዕኳው ካዘጋጃቸው አንድ ክላሽንኮቭ መሣሪያ ከ50 መሰል ጥይቶች ጋር እንዲሁም 2 የተለያዩ ሽጉጦች እና አንድ ተጨማሪ ቢንቶፈ መሣሪያ ከ3 የጥይት መጋዘኖች ጋር ለክልሉ ፖሊስ አባላት ጥቆማ በመስጠት በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን መግለጫው አመልክቷል።ተጠርጣሪው ግለሰብ ለሽብር ተልዕኳው መፈፀሚያ የሚጠቀምበት አይካም የተባለ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚያገናኝ የሬድዮ መገናኛም አብሮ መያዙን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን ብቻ መነሻቸውን የተለያዩ አካባቢዎችን ያደረጉ እና በአሸባሪነት ለተፈረጀው የሸኔ ቡድን እንዲደርሱ ታቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 40,621 የክላሻንኮቭ ጥይቶች፣499 የስናይፐር ጥይቶች፣4525 የብሬን ጥይቶች እንዲሁም የተለያዩ ክላሽንኮቭ መሳሪያዎች፣ስናይፐሮች 50 ሽጉጦችን ጨምሮ የሽብር ቡድኑ በንፁሃን ዜጎቸ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሊጠቀምባቸው ያዘጋጃቸው የተለያዩ ስለታማ ቁሳቁስና ሰነዶች የብሄራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በዳረጉት ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል መያዛቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
በዚህ ህቡዕ የሽብር የግንኙነት መረብ ውስጥ በመሳተፍ ሸቀጦችን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ በተሸክርካሪዎች ነዳጅ ታንከር ውስጥ በመደበቅ፤ሚስጥራዊ ቦታ ሻግ በማዘጋጀት እና መሰል ስልቶችን በመጠቀም የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን በድብቅ ለማሳለፍ የሞከሩ በርካታ የድርጊቱ መሪ ተወናይን አንዲሁም አሸከርካሪዎች፣ረዳቶች እና ሌሎች ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጫ አመልክቷል፡፡
 
ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር በመቀናጀት በኦሮሚያ ክልል አንድ አንድ አካባቢዎች የሀገርንና የህብረተሰቡን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል እየተንቀሳቀሰ ያለውን የሸኔ ቡድን ሴራ ለማክሸፍ እና ቡድኑን ለመደምሰስ እየተወሰደ ያለውን የተቀናጀና ተከታታይ እርምጃ የክልሉ ህዝብ ጥቆማ በመስጠትና ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥ ለጸጥታና ለደኀንነት አካላት ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ እንደ ነበርና ህብረተሰቡ ይሄንን የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.