Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው- የፖለቲካ ተንታኝ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታትና በሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ህወሃት የተለያዩ ጉዳቶችን እያስተናገዱ መሆናቸውን የፖለቲካ ተንታኙ ጄፍ ፒርስ አስታወቀ።
የጄፍ ፒርስ ምንጮች እንደጠቆሙት÷ ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ሄደው በድርጅቶቹ ውስጥ በቋሚነትና በኮንትራት ቅጥር እየሰሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ማንቋሸሸ፣ ድብደባ፣ እስራትና ሌሎች የስነልቦናና አካላዊ ጉዳቶችን እያስተናገዱ ቢሆንም÷ በትግራይ ያሉ የድርጅቶቹ ሃላፊዎች ጉዳዩን ለበላይ ሃላፊዎችም ሆነ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ አልፈቀዱም።
ቡድኑ በሰራተኞቹ ላይ የሚያደርሰው ጥቃት ተባብሶ ከመቀጠሉም በላይ ሰራተኞቹ በሚደርስባቸው ጉዳት ምክንያት ከማረፊያ ጣቢያቸው ወደ ስራ ለመሄድ መቸገራቸውን ነው ምንጮቹ የገለጹት።
አንዳንድ ሰራተኞችም በአሸባሪው ድርጅት ለቀናት ታፍነው ቢቆዩም የተመድና የድርጅቶቹ ሃላፊዎች ጉዳዩን በዝምታ በመመልከት የሰራተኞቹን የእለት ውሎና ችግሮች መዝግበው ለማስቀመጥ ፈቃደኞች አልነበሩም ብለዋል።
እንደ ታማኝ ምንጮቹ ገለጻ÷ የድርጅቱ ዝቅተኛ ሰራተኞች ሳይቀሩ በአሸባሪው ህወሓት በምርመራ ስም መንቋሸሽ፤ ለብዙ ጊዜ መታገትና መንገላታት የደረሰባቸው ሲሆን፥ የባሰ ችግር ሲያጋጥም የሚወሰደው አማራጭ ሰራተኞቹን ወደ አፋርና ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች እንደሚያዘዋውሯቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ክስ ሲያዘንብ የቆየው “ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን” አባላት የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ለቀናት ታግተው ረዥም ጊዜ በወሰደ ድርድር ከተለቀቁ በኋላ፥ ወደ ሌላ ቦታ መዛወራቸው የተገለጸ ሲሆን፥ አሸባሪው ሕወሃት በሰራተኞቹ ላይ ስለሚፈጽመው እንግልት ድርጅቱ ትንፍሽ አለማለቱም ተነግሯል።
በክልሉ ያሉ የተባበሩት መንግስታት ሃላፊዎችም በተመድ ሰራተኞች ላይ የሚፈጸሙ በደሎችን በማጣጣል በዝምታ እያለፏቸው መሆኑን ያስረዱት እነዚህ ምንጮች፥ የራሱን ሰራተኞች መታደግ ያልቻለ ድርጅት ሌሎችን እንዴት ይታደጋል ሲሉም ጠይቀዋል።
በሃገር ውስጥ ጉዳይ በጣልቃ ገብነትና ለሽብርተኛው ቡድን ሲያደርጉት በነበረው ድጋፍ ምክንያት ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረጉት ሰባቱ የተመድ ሰራተኞችና የሥራ ሃላፊዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማሳየት ከበቂ በላይ መሆናቸውን ጄፍ ፒርስ በጽሁፉ መግለጹን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.