Fana: At a Speed of Life!

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት ስራዎች ተሰርተዋል -አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

አምባሳደሩ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል ነው ያሉት።

የአዲሱን መንግስት ምስረታ ተከትሎ ፖላንድ፣ ቤልጀም፣ ፊኒላንድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻይና፣ ቬንዙዌላ፣ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣፣ ሰሜን ኮርያና ሌሎች በርካታ ሀገራት ለመሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል ነው ያሉት።

በ39ኛው የአፍሪካ የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባም ለሀገራት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ገለፃ ተደርጓል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወቅታዊውን የሰላም ችግር ለመቅረፍ አዲስ ፍኖተ ካርታ እንደምታቀርብ መግለጿንም አንስተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት የአውሮፓን ህብረት የተሳሳተ አቋም ለማስተካከል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ከስኖቪኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መወያየታቸውንም ነው የጠቀሱት።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሚያደርሰውን ጥፋት አስመልክቶ እውነታውን አስረድተዋል ነው የተባለው።

አሸባሪው ቡድን ከ420 እርዳታ ጭነው የገቡ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት ተግባር ስለማዋሉም ኢትዮጵያ ለህብረቱ ገለፃ አድርጋለች ነው ያሉት።

ከሲውዲን፣ ከእስራኤልና ከደቡብ ሱዳን ልዑካን ጋር ውይይት መደረጉንም የገለፁት አምባሳደር ዲና የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን የተዛባ አቋም ለማስተካከል የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልፀዋል።

እንዲሁም ጅቡቲ የሚገኙ የአፍሪካ ባለሃብቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውንና በእንስሳት ሃብት ልማት ላይ ከተሰማሩ አካላት ጋር መወያየታቸውን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰቡን ተናግረዋል፡፡

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር በተወሰኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የተስማማን ሲሆን ቀሪው መፍትሄ ከአፍሪካ ህብረት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ሁለተኛው ዙር የዲፕሎማቶች እና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ስልጠና መጠናቀቁንና አገራዊ፥ ቀጠናዊ፥ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ግንዛቤን ለማዳበር የሚያግዝና ሁሉን አቀፍ መስኮችን የዳሰሰ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በሌላ በኩል አምባሳደሩ በማብራሪያቸው በሱዳንና በግብፅ የሚካሄዱ ወታደራዊ ልምምዶች መብት ቢሆንም የኢትዮጵያን የሉዓላዊነት ቀይ መስመር ማለፍ አይችሉም ብለዋል፡፡

ወታደራዊ ልምምዱ ኢትዮጵያን እስካልነካ ድረስ ኢትዮጵያ ጉዳዩ አያስጨንቃትም ፤ሀገሪቱ ከውጭ ሀይሎች ይልቅ ለውስጥ አንድነቷ ትኩረት ትሰጣለች ነው ያሉት።

በተለያዩ ሀገራት የዲፕሎማቶችን ለውጥ ተከትሎ ለዜጎች የአገልግሎት ክፍተት እንዳይጓደል በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።

ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጁ እንደሆነም ገልፀዋል።

በዚህም ከወቅታዊ ችግሮች ይልቅ ለዘላቂ መፍትሄዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብን እንደማስፈራሪያ መጠቀማቸው እውነታውን ካለማወቅ ይልቅ በጥቅም ስሌት ላይ የተመረኮዘ ነው ብለውታል።

ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተተ እይታ እንዲኖረው የሚያደርጉ አካላትም ከእውነታው በተቃርኖ የቆሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ለማለፍ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ፅናት፣ እምቢ ባይነትን በመያዝ ብቻውን ቆሞ ማሸነፍ ይችላል ብለዋል አምባሳደሩ።

በመግለጫቸውም አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት መንግስታትና ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተዛባ አመለካከት መያዛቸውን ጠቅሰዋል።

የተዛባና አድሏዊ አቋማቸው ሆን ብለው የግል ፍላጎትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ጫናቸውን ከመፍራት ይልቅ በጋራ ሆነው “ለአገራቸው ህልውና መቆም አለባቸው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከመጡበት ዓላማ ውጭ የተሰማሩ ግለሰቦችን ማባረሯ መብቷ መሆኑን አንስተው ከዚህ በኋላም ከህግ ውጭ በሰሩት ላይ ትዕግስት የላትም ነው ያሉት።

በመቐለ የተወሰደው እርምጃው ንፁሃንን ኢላማ አለማድረጉን አንስተው ወታደራዊ ማዘዣዎችና የመሳሪያ ማቅረቢያዎች እንደተመቱም አንስተዋል።

በአፈወርቅ እያዩ፣በዘቢብ ተክላይና በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.