Fana: At a Speed of Life!

የተከፈተብንን ጥቃት ለመመከት መፍትሄው የተደራጀ ንቅናቄ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አሸባሪው የጁንታ ቡድን አለኝ የሚለውን ሃይል በማሰባሰብ በአፋርና በአማራ ክልሎች ባሉት ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል።

በዚህ ጥቃት በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል፤ ንብረት ዘርፏል፤የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጋዝ አርከፍክፎ አቃጥሏል፤ በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ አድርጓል።

የተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ እንዳይደርሳቸው አድርጓል።

የሃሰት ፕሮፖጋንዳንም እንደ ዋነኛ መሳሪያው በመጠቀም ላይ ይገኛል።

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ የአማራና አፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሻዎች በመንጋ የመጣውን ጠላት ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመሆን በሚያኮራ መልኩ እየመከቱ ይገኛሉ።

በተለይም ዘራፊው ቡድን በውጫሌ፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦ ደላንታና ጭፍራ ግንባሮች ጦርነት የከፈተ ቢሆንም የጸጥታ ሃይሉና የህብረተሰቡ የጋራ ጥምር ሃይል ይህንን ወራሪ ሃይልና ሰርጎ ገቦችን በጀግንነት እየመከተ ይገኛል።

በሌሎች ግንባሮች ሽንፈትን እያስተናገደ የሚገኘው የጁንታው ቡድን ያለውን ሃይል ሁሉ አሰባስቦ ወደ ወሎ አምጥቷል። ይህ ደግሞ የመጨረሻ ጥረቱ ነው።

አላማውም ህዝቡን ማስጨነቅና ማሸበር እንጂ ማሸነፍ አይደለም። ይህንን የሽብር ቡድኑን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመመከት የደቡብ ወሎና የአፋር ህዝብ በተለይም ወጣቶች እያደረጉ ያሉት አኩሪ ተጋድሎ እጅግ የሚደነቅ ነው።

ለፀጥታ ሃይሎች ደጀን ከመሆን ጀምሮ በየሸጡ የሚሽሎኮሎኩ የጠላት ሃይሎችን በመመከት፤ በየአካባቢው ለስለላ የተሰማሩ ፀጉረ-ልውጦችንና ሰርጎ ገቦችን ተከታተሎ በመያዝ ታሪክ የማይዘነጋው ተጋድሎን እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ጠላት ይህንን የህዝብ አኩሪ ተጋድሎ ጥላሸት የሚቀቡ አፍራሽና ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎችን እየነዛ ነጻ አካባቢዎችን እንደተያዙ በማስመሰል ህዝብን ለማሸበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ህብረተሰቡ በዚህ በጠላት አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳይረበሽ የጀመረውን ሃገር የማስቀጠል ተጋድሎ በተደራጀ ንቅናቄ መመከት፤ አካባቢና ቀዬውንም ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል።

ከጦርነት አካባቢ ውጪ ያሉ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለዚህ ታሪካዊ ተጋድሎ አጋርነታቸውንና ደጀንነታቸውን እንደ እስከዛሬው ሁሉ እንዲያረጋግጡም መንግስት ጥሪ ያቀርባል።

ከመደበኛ የጦርነት አካሄድ በተቃራኒ የመጣን ሃይል ማንበርከክ የሚቻለው የተደራጀ ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.