Fana: At a Speed of Life!

ሁሉም ወደ ወሎ ይትመም፤ ይዝመት ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሽብርተኛው የትህነግ ኃይል የከፈተውን ጥቃት ለመመከት ሁሉም ወገን ራሱን በማደራጀትና በአንድነት በመነሳት ወደ ወሎ መትመምና መዝመት አለበት ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጥሪ አቀረቡ።
ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ ሽብርተኛው ቡድን ባካሄደው ወረራና በፈጸመው ጥቃት ያለማቋረጥ በርካታ ወገን ገድሏል፤ ሕዝብ አፈናቅሏል።
መንግሥትና ሕዝብ የሠራውን መሠረተ ልማት አውድሟል ነው ያሉት። ጥቃቱን መመከት የሚቻለውም ራስን በማደራጀትና በአንድነት በመነሳት ነው ብለዋል።
የሽብርተኛው ቡድን የጥቃት ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስና ምሥራቅ አፍሪካን ማተራመስ መሆኑን ገልጸዋል። ትግሉ የአማራና የአፋር ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ መሆኑን ነው ነው የተናገሩት።
የክልሉ መንግሥት አስቀድሞ ባደረገው የክተት ጥሪ የጠላትን ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች መግታት መቻሉን ነው የገለፁት።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች መመከት መቻሉንም አስታውቀዋል።
በቅርብ ጊዜ የጠላት ኃይል ከጀርባው ብዙ ሕዝብ በማስከተል ትኩረቱን ደሴና ኮምቦልቻ ላይ በማድረግ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቃቱን ለመመከት ጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ከጀግናው የአካባቢው ሕዝብ ጋር ጠላትን እየተፋለመው መሆኑን ገልጸዋል። አኩሪ ጀብዱ እየተፈጸመ መሆኑንም አንስተዋል።
የደቡብ ወሎ ሕዝብ በአንድነት በመትመም ከሠራዊቱ ጋር በመሰለፍ ስንቅ በማዘጋጀት እና ሞራሉን በማነሳሳት የጀግንነት ደጀንነቱን እያረጋገጠ ይገኛልም ነው ያሉት።
ጠላት አሁንም ሕዝብ አሰልፎ እየመጣ ስለሆነ÷ ጠላትን ለመደምሰስ ሁሉም መተባበር ይገባል ነው ያሉት።
ቀደም ሲል የተጠራውን የክተት ጥሪ መነሻ በማድረግ ሁሉም የመንግሥት እና የግል ታጣቂ ሁሉ ወደ ወሎ ይትመም፤ ይዝመት ጥሪ አቅርበዋል።
ሁሉም በጀመረው አግባብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፍ ረገድ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት።
አማራና አፋር ክልል ተጠቅቶ የሚተርፍ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የለምም ብለዋል። መላው የሀገሪቱ ሕዝብ በአንድነት የሚነሳበትና ጠላትን ከሀገር የሚያጠፋበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ ቀደም ሲል የያዘውን አቋም የበለጠ በማጠናከር እና በመደራጀት እንዲዘጋጅም ጠይቀዋል።
የተራዘመ ትግል ስለሚጠይቅ በፅናት እንዲታገልም ጠይቀዋል።
የሕዝባችን እንባ በጀግኖች ትግልና መስዋእትነት ይታበሳል ብለዋል። ጠላትን እንደምናሸንፈው አልጠራጠርም ማለታቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.