Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 366 ሺህ 737 ዜጎች ሁለተኛውን ዙር የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸው ተገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 366 ሺህ 737 ሰዎች ሁለተኛውን ዙር የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በከተማዋ የኮቪድ-19 ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ስራ በሁለተኛው ዙር 366 ሺህ 737 ሰዎች መከተባቸውን÷ በቢሮው የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት ዳይሬክተር ቤተልሔም ታየ ገልጸዋል፡፡

ክትባቱን የወሰዱት 124 ሺህ 919 የአስትራዜኒካ፣ 15 ሺህ 700 ሲኖፋርም እንዲሁም 226 ሺህ 118 የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም 177 ሺህ 602 ዜጎች የመጀመሪያውን ዙር ክትባት ወስደው የሁለተኛውን ዙር ክትባት እየጠበቁ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ስለ ክትባቱ ቀደም ሲል በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሯ÷ በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

ከሃይማኖት አባቶች፣ ከማህበረሰብ ተወካዮችና ከተቋማት ሃላፊዎች ጋር በመሆን የተሰራው ስራም ውጤት በማምጣቱ ማህበረሰቡ የክትባቱን ጠቀሜታ ተረድቶ ሊከተብ መቻሉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ተከታታይ ስራዎችን መስራት እንደሚጠይቅም ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች መምህራንን ጨምሮ የትምህርት ቤቶች ማህበረሰብ አባላት መከተባቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ክትባቱን ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቅድሚያ መሰጠቱን ጠቅሰው÷ በቀጣይ እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ የሆኑ ተማሪዎች እንዲከተቡ እየተሰራ መሆኑን ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ቁጥር አንጻር የክትባቱ አቅርቦት በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣይ የሚገባውን የክትባት መጠን መሰረት በማድረግ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.