Fana: At a Speed of Life!

የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አሸባሪውን ህወሃት ሊያወግዝ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ህዝብ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሩን የመገንባት አኩሪ ታሪኩን በመጠበቅ የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን እኩይ ተግባር ሊያወግዘው እንደሚገባ ተመለከተ።

የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት አመራሮች በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ አወያይተዋል።

በጽህፈት ቤቱ የድርጅት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገብርፃዲቅ ገብርመድን በውይይት መድረኩ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ በህዝብና ሀገር ላይ የጥፋት ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል።

የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ሴራ ሳይታለል እንደሌላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሩን በመገንባት ላይ ያለውን አኩሪ ታሪክ መጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ስትኖር ብቻ ነው የትግራይ ህዝብ ህልውና የሚኖረው፤ ችግሮች ካሉ በውይይት መፍታት ይቻላል፤ህዝቡም የህወሓት የሽብር ቡድንን እኩይ ሴራ በመገንዘብ የጥፋት ድርጊቱን ሊወግዝ ይገባል ብለዋል፡፡

የሰሜን ዕዝን በክህደት የጨፈጨፈው ዘራፊና ማፈያ የህወሓት ቡድን የትግራይ ህዝብን እንደማይወክል አውስተዋል።

አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነት አውዳሚ መሆኑን ቢገነዘብም የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ ሲባል ቡድኑን የማስወገዱ ስራ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የጋምቤላ ክልል የመንግስት ተጠሪ አቶ ላከደር ላክባክ በመድረኩ እንደተናገሩት÷ የህወሓት የሽብር ቡድን የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት የማይቀበል የአሽብር ቡድን ነው።

ለዚህም ማሳያው ባለፈው 27 ዓመታት ጋምቤላ ጨምሮ አራቱ ክልሎች አጋር ተብለው ከለውጡ ወዲህ ፓርቲያቸው ሲዋሃድ አፈንግጦ መውጣቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ሀገር እናፈርሳለን የሚለው አስተሳሰብ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸው አሁንም ቢሆን ሀገር ለማፍረስ የተቃጠውን ችግር ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.