Fana: At a Speed of Life!

የአመልድ ዋና ዳይሬክተርና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ለተፈናቃዮች ድጋፍ በሚደረግብት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ በሚደረግበት አግባብ ላይ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ጋር ተወያዩ፡፡
 
አምባሳደር ጊታ ፖሲ ከተለያዩ የሰሜን ወሎ እና ዋግኸምራ ዞን አካባቢዎች ተፈናቅለው በባህር ዳር ዘንዘልማ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
 
ዶክተር አለማየሁ ዋሴ ከአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ፣ ከአሜሪካ ተራዳኦ ድርጅት ምክትል አስተዳዳሪ ሳራ ቻርለስ እና ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ከሚሽን ዳይሬክተር ጋር የተወያዩ ሲሆን፥ ለተፈናቃዮች መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን በጋራ ለማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
 
በዚህም የሽብር ቡድኑ በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
 
ተፈናቃዮቹ በደሴ፣ በባሕር ዳር፣ በኮምቦልቻ እና ሌሎች ከተሞች ውስጥ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ለማህበራዊ ቀውስ ተዳርገዋል ነው ያሉት፡፡
 
ተፈናቃዮቹ የዕለት ምግብ፣ መድሃኒት እና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶችን እያገኙ አለመሆኑንም አብራርተዋል፡፡
 
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በክልሉ ላለፉት 20 ዓመታት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ይሁን እንጂ አሁን ላይ በጦርነት ሳቢያ ተፈናቅለው በስደተኛ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ያሳዩት ድጋፍ አነስተኛ፥የዘገየና እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
አምባሳደር ጊታ ፓሲ በበኩላቸው፥ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ያለምንም አድልኦ የዕለት እርዳታ ለማቀረብ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን ማለታቸውን ከአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ኢትዮጵያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.