Fana: At a Speed of Life!

የመረጠንን ህዝብ አደራና ሃላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ ተግባራት በማከናወን የመረጣቸውን ህዝብ አደራና ሃላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል።
 
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት አቶ ኦርዲን በድሪ ቃለመሃላ በፈጸሙበት ወቅት እንደተናገሩት÷ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚጎለብቱ የተለያዩ ተግባራትን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል።
 
ባለፉት ሶስት ዓመታት በክልል ደረጃ በተጀመረውን ስር ነቀል ለውጥ ሂደት የታዩ ጥንካሬዎችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በመቅረፍ ህዝቡ የሚጠብቀውን በእኩልነት ላይ የተመሰረት ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
 
በህዝቦች እኩልነት፣ የጋራ ተጠቃሚነትና አንድነት ላይ የተመሰረተ መዋቅራዊ ለውጥ ለማረጋገጥ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች በሚካሄዱት ተከታታይ እንቅስቃሴዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እና የክልሉ ነዋሪ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ትርጉም ባለው ሁኔታ ተሳታፊ ለማድረግ ይሰራልም ነው ያሉት።
 
“በአሁኑ ወቅት የሀገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ለመጠበቅ የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ታሪካዊ ተጋድሎ በላቀ አንጸባራቂ ድል ለማጠናቀቅ የተጀመረውን ደጀንነትና አጋርነነት ይበልጥ በማጠናከር አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ያለዕረፍት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
 
የክልሉን አርሶ አደር ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አዲስ የተቋቋመው ምክርቤትና መንግስት በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
 
በተለይም የወጣቶች፣ የሴቶችና የአጠቃላይ የህዝቡን ሥራ አጥነት ለመቅረፍና የኑሮ ውድነትን ትርጉም ባለው ደረጃ ለመፍታት በተጨባጭ ጥናት ላይ የተመሰረቱ ተከታታይ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም አብራርተዋል፡፡
 
ሥርዓትና አመራር ቢለዋወጥ የማይዛነፍ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለህዝባችን መብት መረጋገጥ ዘብ የሚቆም የጸጥታ መዋቅርና ኃይል ለመገንባት የተጀመሩ ተግባራትም ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
 
ህገወጥ የመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታን እንዲሁም ሌብነትን በቁርጠኝነት ለመከላከል ቆራጥ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው ርዕሰ መሰተዳደሩ የገለጹት።
 
የምክር ቤት አባላትና በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃ የሚገኘው አመራር እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ህዝብ የጣለባቸውን አደራ እንዲወጡና ለገቡት ቃል እንዲታመኑ አሳስበዋል።
 
የክልሉ መንግስት በሚያከናቸው ተግባራት ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር መጠየቃቸውንም ከሀረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.