Fana: At a Speed of Life!

የእርዳታ አውሮፕላኖች ከመቀሌ የተመለሱት በስፍራው በሚገኙ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ በመከልከላቸው ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው ዕለት የእርዳታ አውሮፕላኖች ከመቀሌ ሳያርፉ የተመለሱት በአየር ጥቃቱ ሳቢያ ሳይሆን በስፍራው በሚገኙ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፈቃድ በመከልከላቸው መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጉዳዩ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ትናንት የኢፌዲሪ አየር ሃይል በመቀሌ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የወታደራዊ ማሰልጠኛና ማዘዣ ማእከል የሆነውና የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ማሰልጠኛ የነበረውን ቦታ በአየር መደብደቡን አስታውሷል፡፡
 
በዚሁ ዕለት ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በኩል ፈቃድ የተሰጣቸው ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ አውሮፕላኖች በመቀሌ እንዲያርፉ በስፍራው ካሉ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውንም ጠቁሟል፡፡
 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ አውሮፕላኖቹ ከፌደራል መንግስት ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆኑና ወደ አዲስ አበባ የተመለሱትም በኤርፖርቱ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ፍቃድ በመከልከላቸው ብቻ መሆኑንም አሳውቀዋል ነው የለው መግለጫው፡፡
 
ይሁን እነጂ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የእርዳታ አውሮፕላኖቹ የተመለሱት በየአየር ጥቃቱ ሳቢያ እንደሆነ በማስመሰል የተሳሳተ ዘገባ ማሰራጨታቸውን ጠቅሷል፡፡
 
የአየር ጥቃቶቹ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተወሰዱና የሽብር ቡድኑ ለእኩይ አላማ የሚጠቀምባቸውን የመገናኛና የወታደራዊ ማሰልጠኛዎችን ብቻ ኢላማ ያደረጉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
 
የሽብር ቡድኑ ይህንን መሰል የተሳሳቱ መረጃዎችን በማውጣት ህብረተሰቡን በሃሰተኛ ምስሎች ለማወናበድ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተገንዝቦ ጥንቃቄን መውሰድ እንዳለበትም ድርጅቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.