Fana: At a Speed of Life!

ለሸገር ዳቦ ከ309 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ድጎማ እንዲደረግ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲሱ ካቢኔ አንደኛ አመት የመጀመሪያ ሰብሰባውን በማካሄድ የተለያዩ ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡
 
በዚህ መሰረትም :-
 
1. የአዲስ አበባ የመዋቅራዊ ጥናት ማሻሻያ ላይ በዋናነት መሠረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች ለሚነሳባቸዉ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት እና በተለይም በመንገድ ግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት ፣በህንጻ ከፍታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እና በአጠቃላይ በከተማዋ የፕላን ትግበራዎች ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም በሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።
 
2. በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማቃለል ለተለያዩ ተቋማት የበጀት ድጎማ እንዲደረግ ካቢኔው ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ለሸገር ዳቦ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ 309ሚሊየን 337ሺህ 500 ብር ድጎማ እንዲዉል የወሰነ ሲሆን÷ በተመሳሳይም የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነዉ ሆራይዘን ፕላንቴሽን የ199 ሚሊየን 837 ሺህ 500 ብር ድጎማ የሚያደርግ ይሆኗል።
 
በተጨማሪም የተማሪዎች ምገባ የዋጋ ማሻሻያ ሰነድ ላይ ውይይት በማድረግ ለ2014 የትምህርት ዘመን 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ወስኗል።
 
በተያያዘም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የመዋጮ መጠን እንዲወሰን እና በከተማዋ ከ231 ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ዉስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት ለመስጠት የ 144 ሚሊየን ብር ድጋፍ በአስተዳደሩ እንዲደረግ ወስኗል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር የሚያስችል የ70 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግለት ካቢኔ ከውሳኔ ላይ የደረሰ ሲሆን÷ የስፖርት ቡድኑ በዘላቂነት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረዉና በፋይናንስ የራሱን የገቢ ምንጭ መፍጠር የሚያስችለው የተለያዩ አማራጮችን እንዲፈጥር ከውሳኔ ላይ ደርሷል።
 
በመጨረሻም በሀገሪቱ ለተለያዩ አካባቢዎች ለማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጊዜአዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር አቅጣጫ ማስቀመጡን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.