Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች በቀጠናው ተሰማርቶ የሚገኘውን ሰራዊት የሚደግፍና በዞኑ የሚገኘውን አጥፊ ቡድን ደግሞ የሚያወግዝ ሰልፍ አካሂደዋል።

የመተከል ዞንን ሰላም ለመመለስ ተሰማሮቶ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ሃይሎችና ሚሊሻ አባላትን የጀመሩትን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነዋሪዎች በድጋፍ ሰልፉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የህወሓትን ሴራ ተቀብለው ቀጠናውን እያተራመሱ የሚገኙ የጉሙዝ ብሄረሰብን እንደማይወክል የብሄረሰቡ ተወላጆች በድጋፍ ሰልፉ ላይ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የግልግል በለስ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ውባልታ እንዳሉት÷ የጉሙዝ ብሄረሰብን ሽፋን በማድረግ ቀጠናውን እያወኩ የሚገኙ አጥፊዎችን ከማህበረሰቡ በመለየት እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ተግባርን ለማበረታታት ያሳያችሁትን ድጋፍ አጠናክራችሁ በማስቀጠል ለሰላም ዘብ መቆም አለባችሁ ብለዋል።

ለዘመናት የጋራ ዕሴት መስርተው ሲኖሩ የነበሩ ህዝቦችን የብሄር ታርጋ በመለጠፍ የእርስ በእርስ ግጭት በመፍጠር ቀጠናው እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ሃይሎችን ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ የ7ኛ ሜካናይዝድ ጦር ዋና አዛዥና የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ተወካይ ኮሎኔል በስፋት ፈንቴ ተናግረዋል።

በዞኑ ህግን ለማስከበር የተጀመረው ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ኮሎኔሉ÷ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለምንም ስጋት ለማጠናቀቅ ሰራዊቱ ሁልጊዜ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ ሃይሎች ሲፈልጉ በሃይማኖት፣ ሲያሻቸው በብሄር በመከፋፋል ሲሰራ የነበረው ሴራ በመገንዝብ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ከወጣቱ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አሳስበዋል።

ሽፍታው ቡድን የጉሙዝ ብሄረሰብን አይወክልም፤ ሽፍታ ሀገር አይመራም፤ የተጀመረው ኦፕሬሽን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ የጁንታው ተላላኪ አጥፊዎችን መንግስት በአጭር ጊዜ እርምጃ ሊወስድ ይገባል የሚሉት በድጋፍ ሰልፉ የተንጸባረቁ መልዕክቶች መሆናቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.