Fana: At a Speed of Life!

ካፍ ያስተላለፈው ውሳኔ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ካፍ በባህርዳር ስታዲየም ያስተላለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ እና እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲል የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
ካፍ ለእገዳው በምክንያትነት ካነሳቸው አስተያየቶች መካከል÷ የተጨዋቾች መልበሻ ክፍል ግብዓቶችን ማሟላት፣ የቪ አይ ፒ ጣራ ስራ፣ የሚድያ ክፍል ማዘጋጀት፣ የተጠባባቂ ተጨዋቾች መቀመጫ፣ እንዲሁም የሜዳ ሳር እንዲቀየር የሰጠው አስተያየት አግባብነት የሌላቸው አስተያየቶች ናቸው ሲሉ በክልሉ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንታምላክ ሙላት ገልፀዋል።
ስታድየሙን ጣራ ማልበስ፣ በምሽት ጨዋታወችን ማካሄድ የሚያስችል የመብራት (ፍሉድ ላይት) ስራ፣ የተመልካቾች መቀመጫ ወንበር እና የስርዓተ ድምፅ ግብዓቶችን ማሟላት ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁና ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ በመሆናቸው በክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አማካኝነት ከሚመለከተው አካል ጋር እየተመከረበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ካሳ በበኩላቸው÷ የባህርዳር አለም አቀፍ ስታድየም ለበርካታ አመታት የተለያዩ ዓለምዓቀፍ ጨዋታወችን በማስተናገድ ለአገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመው÷ ስታዲየሙ ደረጃውን እንዲያሟላ ካፍ ከሰጣቸው አስተያየቶች መካከልም በክልሉ አቅም ሊሸፈኑ የሚችሉትን ለመስራት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በቀጣይም ስታድየሙ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች በማሟላት አለም አቀፍ ደረጃውን አሟልቶ ወደ ውድድር አንዲመለስ የሁሉም አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ÷ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ መጠየቃቸውን ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.