Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል የወተት ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን የሚተገበረው የወተት ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ተደረገ፡፡
ፕሮጀክቱ አለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ከቪ ኤስ ኤፍ ድርጅት ጋር በመተባበር የሚጀመር ሲሆን÷ በፋፈን ቀብሪበያህ እና ጅግጅጋ ወረዳዎች የሚተገበር ነው ተብሏል።
አለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት፣ የቪ ኤስ ኤፍ ድርጅት ተወካዮች ፣ የሶማሌ ክልል የማህበራት ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር ሼክ አብዲን ጨምሮ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት ፣ ከክልሉ የእንስሳትና አርብቶአደር ልማት ቢሮ እና ከፋፈን ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አካላት በተገኙበት የወተት ልማት እሴት ሰንሰለት የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያና የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
የአለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የፕሮስፔክት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ጂን ይቪስ ባርባ÷ በፋፈን ዞን የሚተገበረው የወተት ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ስደተኞችንና ስደተኞች ተቀባይ የህብረተሰብ ክፎሎችን ህይወት ለማሻሻል የሚተገበር መሆኑን ገልፀዋል።
ኃላፊው ፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ዝቅተኛ የሆነውን የወተት ምርት መጠንን ለማሳደግና ህብረተሰቡ ከወተት የሚያገኘው ገቢ እንዲጨምር ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል የማህበራት ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር ሼክ አብዲ ÷ አለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት ይፋ ያደረገው የወተት ምርት እሴት ሰንሰለት ኑሮው በእንስሳት ላይ ለተመሠረተው የአካባቢው ህብረተሰብ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
በቀብሪበያህ እና ጅግጅጋ ወረዳ የሚተገበረው የወተት ገበያ ልማት ፕሮጀክቱ ማህበራትን በማደራጀት ፣ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ስደተኞችን እና ስደተኞችን ተቀባይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመድረኩ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ አለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት የወተት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት፣ በፋፈም ዞን የሚካሄደው የወተት ልማት እሴት ሰንሰለት ስራዎች ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው የሶማሌ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.