Fana: At a Speed of Life!

የሽብርተኛው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሠራዊቱን የድል ግስጋሴ አይገታውም-መከላከያ ሰራዊት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብርተኛው ህወሓት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሠራዊቱን የድል ግስጋሴ አይገታውም አለ የመከላከያ ሰራዊት፡፡
 
የመከላከያ ሰራዊት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷አሸባሪው ህወሓት ከሚታወቅባቸው ስልቶቹ መሀል አንዱ ቅጥፈቱ መሆኑን አስታውሷል፡፡
 
ቡድኑ ጉልበት ሲያንሰው ምላሱ ይረዝማል፤ ያልሆነውን ሆንኩ፣ ያላደረገውንም አደረኩ ይላል፤ ይህ ደግሞ ጥርሱን የነቀለበት እና ተወልዶ ያረጀበት ባህሪው መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡
 
አንድም ቀን ከአፉ እውነት ተገኝታ የማታውቀው ይህ ሽብርተኛ፣ ሽንፈቱን የሚሸፍነው የሠራዊቱን ስም በማጠልሸት ነው ያለው መከላከያ ሰራዊቱ÷ደጋፊዎቹ ኪሳራውን እንዳያውቁ፣ ሰላማዊው ህዝብ ልጆቹን እና ምግብ እንዳይጠይቅ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነውረኝነቱን እንዳይገነዘብ ሁል ጊዜ የተለመደ ስልት አለው ፤ይህም የሠራዊቱን ስም ማጠልሸት መሆኑን ጠቁሟል ፡፡
 
ጀግናው ሠራዊት ባልዋለበት እና ባህሪው ባልሆነው ጉዳይ በጁንታው ፕሮፓጋንዲስቶች በስሙ ተደጋጋሚ ድራማ እየተሰራበት አይተናል ፣ ሰምተናል ፤ እዚህ ቦታ ሰላማዊ ህዝብ ገደል ከተተ፣ እዛ ደግሞ አቃጠለ የሚሉ በውሸት ተቀነባብረው ለዓለም የደረሱ ተውኔቶችን ታድመናል ሲልም አስታውሷል፡፡
 
እነዚህ በተደጋጋሚ በመከላከያ ላይ ሲደረጉ የነበሩት የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ልክ ጸሀይ እንደመታው የጠዋት ጤዛ ወዲያው እውነታው ታውቆ ይጋለጣሉ ያለው ሚኒስቴሩ ÷ ለጊዜው ደጋፊዎቹን ቢያስጨፍርም የኋላ ኋላ እውነቱን ህዝቡ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተገነዘቡት መምጣታቸውን አውስቷል፡፡
 
መዋሸት የማይሰለቸው ይህ ቡድን አሁንም የሠራዊቱን ስም ለማጥቆር በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፤ በዚህም ሠራዊቱ ንጹሃንን ገደለ፣ አረደ የሚሉ ከብት ባልዋለበት አይነት ድራማ ለማሳየት በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
 
ይህም እንደ ከዚህ ቀደሞቹ እርቃኑን መቅረቱ አይቀርም ፤ ምክንያቱም ቅጥፈትን የሚሸከም ህዝብ ስለሌለን ነው ያለው፡፡
 
የመከላከያ ሠራዊት ሰብዓዊ ስሜት ያለው ህዝባዊነቱን ዛሬ ዛሬ አሸባሪው ህወሓት ቢክድም ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ህዝብ ሲቸገር የሚያካፍል፣ ሲታመም የራሱን መድሀኒት የሚሰጥ፣ ህዝብ ሲጠማ የሚያጠጣ፣ ሊገሉት የመጡት ሲማረኩ እንኳን የራሱን ሬሽን አካፍሎ ጦሙን የሚውል አዛኝ ሩህሩህ እና ደግ ሰራዊት መኖሩንም አንስቷል፡፡
 
የሠራዊቱ ባህሪ ይህ ሆኖ ሳለ የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች ሰሞኑን የተለመደ የፈጠራ ስራ እየፈበረኩ በማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጩት የሠራዊቱን የደንብ ልብስ በመጠቀም በተደመሰሱት ታጣቂዎቹ ላይ የሚፈጸመው የተለመደው ድራማ መሆኑን ህዝቡ እንዲረዳ እየገለጸ ሠራዊቱ ወደፊትም የጀመረውን ሽብርተኞችን የማጽዳት ዘመቻ ከግብ ያደርሳል ብሏል በመግለጫው፡፡
 
ምንም እንኳን ጠላቶች በሰራዊቱ ያልዋለበትን እና ባህሪው ያልሆነውን ጭቃ ሊለጥፉበት ቢሞክሩም፣ እሱ ግን እንደ እስካሁኑ ለእውነት እና ርትዕ በመቆም የድል ግስጋሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል ማለቱን ከመከላከያ ሰራዊቱያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.