Fana: At a Speed of Life!

ሱዳናውያን ችግሮችን በራሳቸው አቅም የመፍታት ችሎታ አላቸው ብለን እናምናለን – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱዳናውያን አሁን ላይ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ችግር በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ እምነታቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በዓረብኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት÷የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ በሱዳን የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊ እና የጠበቀ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለአብነትም የታላቁ አባይ ወንዝ ስልጣኔ ባለቤት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሀገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ለማድረግ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ትልቅ ሚና መጫወቷን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ መውጫ መንገድ እንዳለ ያለንን እምነት እና ተስፋ በምንገልጽበት በዚህ ወቅት፤ የፖለቲካ ልዩነቶች መስፋት እና የችግሮች መባባስ ስጋት እንዳለብንም መግለጽ እንሻለን ብለዋል፡፡

የሕገ መንግስታዊ ሰነዱ ቃል ኪዳን እሴቶች ለማስጠበቅ እና የጁባ ሰላም ስምምነት ነጥቦችን በማስከበር የሱዳን ሕዝቦችን ብሩህ የሆነ መጻኢ ጊዜ ተስፋን ዕውን ለማድረግ የሱዳን ሀገር በቀል ጥበብ ልምዶች በቂ የሆነ አቅም አላቸው ብለን በጽኑ እናምናለን ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና በአጠቃላይ በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እያለፈ በሚገኝበት እና ተግዳሮቶች እየሰፉ በመጡበት በዚህ ወቅት ከሱዳን ሕዝቦች ጎን በሙሉ ልባችን የምንቆም መሆናችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡

ከዚህም ባሻገር በቀጠናችን የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ለሉዓላዊና ነጻ ውሳኔዎቻችን ያነሰ ግምት በመስጠት ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚጥሩ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.