Fana: At a Speed of Life!

በአማራና በአፋር ክልሎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና በአፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች በተፈጥሯዊ አደጋ ለተፈናቀሉና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁሟል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ እንደገለጹት፤ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉና ችግር ለገጠማቸው ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ድጋፉም የዕለት ደራሽ ምግብና የዓይነት ድጋፎች የሚያካትት መሆኑን ጠቁመው፤ ድጋፉም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየቀረበ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል የተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 945 ሺህ መድረሱን አመላክተዋል።

ከእነዚህም መካከል 459 ሺህ 763ዎቹ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ ተፈናቃዮቹን ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት 122 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ወደ ሥፍራው እንዲላክ መደረጉን በመጠቆም።

በተመሳሳይ በአፋር ከ265 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቁመው፤ እስካሁን ባለው ሂደት 35 ሺህ 637 ኩንታል እህል ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የሰብዓዊ እርዳታውን የሚያስተባብሩ ማዕከላትን በማቋቋም ድጋፉን በተሳካ መልኩ ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በተከሰተ የድርቅ አደጋ ምክንያት 160 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸው፤ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው መሆኑን ተናግረዋል፤እስካሁን ባለው ሂደት 27 ሺህ 900 ኩንታል እህል ለተረጂዎች መድረሱን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎችን የሚቀርበው ድጋፍ 70 በመቶ የሚሆነው በመንግሥት የሚሸፈን መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.