Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት ግመሎቻችንን ጭምር ጨፍጭፏል -የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አሸባሪው ህወሓት የአፋር ህልውናን ለማጥፋትና ለህዝባችን ያለውን ንቀት ለማሳየት ግመሎቻችንን ጭምር ጨፍጭፏል” ሲሉ በአፋር ክልል የሰመራ ሎጊያ ነዋሪዎች ገለጹ።
አሸባሪው ህወሓት በአፋር ህዝብ ላይ ዳግም ጥቃት ማድረሱ ቡድኑ ካለፈው ስህተቱ የማይማርና ከጨካኝነቱ የማይላቀቅ ኢሰብዓዊነት የተጠናወተው ስብስብ እንደሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ቡድኑ በንፁሃን ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ህፃናትና እናቶችን ከመግደሉ ባሻገር “የአፋር ህዝብ እንደ ልጆቹ በሚያያቸው ግመሎቹ ላይም ጭፍጨፋ ፈፅሟል” ብለዋል።
አሸባሪው ህወሃት በአፋር ህዝብ ዘንድ እንደ ትልቅ የሀብትና የክብር መገለጫ የሆነውን ግመል በመግደል ለአፋር ህዝብ ያለውን ጥልቅ ጥላቻ ማሳየቱንም ተናግረዋል።
የአገር ሽማግሌው አቶ ሀሰን ሁሴን አህመዶ ግመሎች በአፋር ህዝብ ዘንድ “ግመል ወተቱም ስጋውም መድሃኒት ነው” ተብሎ ትልቅ ክብር እንደሚሰጠው ነው የተናገሩት።
የአፋር ህልውና ከግመል ጋር እጅጉን የተቆራኘ መሆኑን አመልክተው፤ አንድ ግመል ያለአግባብ ሲገደል በሽማግሌዎች በምትኩ 12 ከብት እንደሚጠየቅና መስጠትም ግዴታ መሆኑን ይናገራሉ።
“ግመል ለአፋር ትልቁ ሀብቱ ነው” የሚሉት አቶ አህመድ ኢሴ “አፋሮች ግመል ከሌለን ህይወት የለንም” ብለዋል።
ወጣት አህመድ ወሌ ደግሞ ግመል አንድ አባት ለልጁ የሚያወርሰው ትልቁ ሀብቱ መሆኑን ገልፆ፤ ግመል ለአፋር ህዝብ ትልቁ የኢኮኖሚ አውታሩ መሆኑን ይናገራል።
የአገር ሽማግሌው አቶ ሀሰን ሁሴን አህመዶ አሸባሪው ህወሓት የአፋር ግመሎችን የጨፈጨፈው ኢኮኖሚውን አድቅቆ ህዝብን የበለጠ ደሃ ለማድረግ ጭምር እንደሆነም ገልጸዋል።
ወጣት አህመድ ወሌ ደግሞ እንደገለጸው፤ አሸባሪው ቡድን የአፋር ህዝብን መለያ ግመሉን በመጨፍጨፍ ትዕግስቱን የሚፈታተን ጥቃት ፈጽሟል።
አቶ አብዱ ያሲን የተባሉ ነዋሪ “አሸባሪው ቡድን ሰው ይፈጽመዋል ተብሎ የማይገመት የጥፋት ተግባር በመፈፀም የፈሪ ተግባሩን አሳይቷል” ብለዋል።
ይህ ተግባሩ የአፋርን ህዝብ ያስቆጣ በመሆኑ አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
“በውሸት ወሬዎች ሳንደናገር ለማንነታችንና ለክብራችን በአንድነት በመታገል አረመኔውን ቡድን ለመቅበር ተዘጋጅተናል” በማለት ገልጸው፤ ቡድኑን ድል በማድረግ የአባቶች ገድል ዳግም እንደሚፈጸም ጠቅሰዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.