Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንትን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒተር ሞረርን በትናንትናው ዕለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገረዋል፡፡

በወቅቱም ፕሬዚዳንቱ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ባለው የረጅም ጊዜ አገልግሎት ፤ በመንግስት በኩል እየተደረገለት ስላላው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ በገለልተኝነት መርህ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን በማስታወስ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ÷ በተለይም በትግራይ ክልል እያደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የአየር በረራ ፈቃድ፣ የጥሬ ገንዘብ መጠን መጨመር እና የነዳጅ ፍላጎትን በተመለከተ መንግሰት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር ከሰብዓዊ ዕርዳታ በተጨማሪ በጤና ፣ በዘላቂ ልማት፣ የተለያዩ ቤተሰቦች በማገናኘት እንዲሁም እስረኞችን በመጎብኘት የስራ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም አብራረተዋል፡፡

የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በርካታ ዜጎች ድርጅታቸው የድጋፍ መጠኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በበኩላቸው ÷ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ ፤ በሰብዓዊነት መርህ ተልዕኮውን ለመወጣት እየሰጠ ስላለው አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ድርጅቱ በትግራይ ክልል እያደረገ ካለው የሰብዓዊ ድጋፍ ጋር ተያይዞ በትክክለኛ ፍላጎት ላይ በመመስረት የነዳጅም ሆነ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት እንዲሟላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

ህወሓት በከፈተው ወረራ ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎችን ተጨማሪ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በተያያዘም አቶ ደመቀ ÷ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ያሉትን የጦር እስረኞች በተመለከተ ታሳሪዎቹ ዜጎቻችን ከመሆናቸውም ባሻገር የዓለም አቀፍ ህግን ታሳቢ በማድረግ ተገቢው አያያዝ ይደረግላቸዋል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.