Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላምና መረጋጋት እንደ ራሷ ሰላም ታየዋለች-ዛሂድ አል-ሀረሪ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላምና መረጋጋት እንደ ራሷ ሰላም አድርጋ ታየዋለች ሲሉ የኢትዮጵያና ዓረብ ሀገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛሂድ ዘይዳን አል-ሀረሪ ገለጹ።
 
የሱዳን ሕዝብ ችግር ባጋጠመው ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያውያ ሁሌም ከጎናቸው መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
 
የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ የሲቪል መንግስቱን በትኖ ስልጣን በመያዝ በሀገሪቷም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡
 
የኢትዮጵያና ዓረብ ሀገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛሂድ ዘይዳን አል-ሀረሪ ÷ኢትዮጵያና ሱዳን በደም የተሳሰረና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
 
ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ የተሳሰረና በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አብራርተዋል።
 
በመሆኑም “ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላምና መረጋጋት እንደ ራሷ ሰላም አድርጋ ታየዋለች” ነው ያሉት።
 
ሱዳን ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያ ከጎኗ በመሆን ያላትን ወዳጅነት በተግባር ማሳየቷንም ነው ያነሱት፡፡
 
እ.አ.አ በ2019 የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አል-በሽር በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ከወረዱ በኋላ የተፈጠረው አለመረጋጋት በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና መጫወቷንም ነው ተመራማሪው ያወሱት።
 
በወቅቱ ሱዳን ያጋጠማትን ችግር በመፍታት ረገድ ተሳትፎ ለማድረግ በርካታ ሀገራት ጥያቄ ቢያቀርቡም የሱዳን ሕዝብ ግን ኢትዮጵያን አምኖ መምረጡን ተናግረዋል፡፡
 
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሱዳን ጉዳይ በተመለከተ አምባሳደር መሐሙድ ድሪርን ልዑክ አድርገው በመላክ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።
 
ኢትዮጵያ የሱዳንን ሰላምንና መረጋጋት እንደ ራሷ ሰላም አድርጋ ታየዋለች፤ ኢትዮጵያ ሕዝብም ሱዳናውያን ሰላም እንዲሆኑ አጥብቀው ይሻሉ ብለዋል፡፡
 
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ትናንት ያወጣው መግለጫ የዚሁ ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል።
 
የሁለቱ ሀገራትና ሕዝቦች ለረጅም ጊዜያት የቆየ ግንኙነት በተለያዩ አገራት ፍላጎት እንደማይሻክርና የኢትዮጵያና ሱዳን ሰላም መሆን የሚጠቅመው ሁለቱን ሀገሮች ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በሱዳን ያሉ ለውጦች የሚያመጡትን ውጤት በቅርበት መከታተልና ለለውጦቹ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባትም አመልክተዋል።
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.