Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሬድዋን ከኢኮስ ብረታ ብረት ኩባንያ ሃላፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማራው ኢኮስ ብረታ ብረት ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሼል ኤችቾ ጋር ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም ኩባንያው በፈረንጆቹ ከ2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ በብረታ ብረት የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
 
ኩባንያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ከተሰማሩት የኮሪያ ባለሃብቶች አንጋፋ እና ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን አንስተው÷ የማምረት አቅሙን በሙሉ ተጠቅሞ ለማምረት እንዲችል የመንግስትን ተጨማሪ እገዛ ጠይቀዋል።
 
በተጨማሪም ኩባንያው ሌሎች የኮሪያ ባለሃብቶችን ወደ ሀገራችን ለመሳብ በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት የሚሰማሩ ኩባንያዎችን መረጃ እያደራጀ እንደሚገኝ እና በዚህ ረገድም ሴዑል ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆዩቱን ጠቁመዋል፡፡
 
የኢንቨስትመንት ውጥናቸው የተሳካ እንዲሆንም በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ሚስተር ሼል ጠይቀዋል፡፡
 
በሌላ በኩል ኩባንያው ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ትልልቅ የኮሪያ ኩባንያዎች ተሳታፊ የሚያደርግ የኮሪያ የግብርና ማሽነሪዎች ኤግዚቢሽን በዱከም ለማካሄድ እየሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
 
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው÷ኩባንያው በሀገራችን እያደረገ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚበረታታ ነው ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የኩባንያው የኢንዱስትሪ ፓርክ የማልማት ዕቅድም ተግባራዊ እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደግለት ገልጸው÷ የሚመለመሉ ባለሃብቶች አቅም ያላቸው፣ ቴክኖሎጂን ማሸጋገር የሚችሉ እና ለሌሎች ባለሃብቶች አርአያ መሆን የሚችሉ እንዲሆኑ ጠቁመዋል፡፡
 
ከኩባንያው ጋር የኢንቨስትመንት ሂደቱን በተመለከተ መረጃ በመለዋወጥ ቀጣይነት ያለው የክትትል ሥራ እንደሚሰራ እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.