Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ13 ሚሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል የ2013 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ስራ መከናወኑን የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ገለጸ፡፡
 
በክልሉ የ2013 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመዝጊያና የ2014 ዓ.ም የበጋ ወር የበጎ ፋቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
 
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ደሊላ ዩሱፍ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ በ2013 ዓ.ም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡
 
በተከናወነው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች በንቃት መሳተፋቸውን ጠቁመው ÷ በዚህም ወጣቶች እውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል፡፡
 
በቀጣይ በሚከናወነው የበጋ ወር የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይም የተሻለ ስራ ለመሥራት ሁሉም መንቀሳቀስ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡
 
በ2013 ዓ.ም የክረምት ወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራት በብር ሲገመት 13 ሚሊየን ብር በላይ የሚደርስ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
 
የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም በበኩላቸው ÷ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መሳተፍ ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በአገልግሎቱ ለሚሳተፉ ወጣቶች ልምድና ክህሎት ለመቅሰም ያግዛል ብለዋል።
 
በተለይም ወጣቱ ትውልድ በበጎ ፍቃድ ተግባር ተምሳሌት መሆን ይገባል ያሉት ወይዘሮ አሚና ÷ይህም በተለይ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አረጋውያን፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ከመርዳት አንፃር ጉልህ ድርሻ አለው ነው ያሉት።
 
በመጨረሻም በ2013 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የወጣት አደረጃጀቶችና አመራሮች የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
 
በመርሃ ግብሩ ላይም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የበጎ ፍቃደኞች ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.