Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ሕዝብ ነጻነቱን የሚያስከብረው በክንዱ ነው – የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ሕዝብ ነጻነቱንና ፍትህን ማግኘት የሚችለው በክንዱና በመስዋእትነት ነው አሉ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀንበር ፡፡

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ከአሚኮ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ባደረጉት ቆይታ የአማራ ሕዝብ በጥንተ ጠላቱ ትህነግ ዛሬም የተለያዩ በደሎች እየደረሱበት ነው፡፡

ለዓመታት በኢትዮጵያ ስልጣነ መንበር ላይ የቆየው አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ስብስብ በአማራ ላይ እልፍ በደሎችን ፈጽሟል፤ ዛሬም መፈፀሙን ቀጥሏል ብለዋል፡፡

በመዋቅር የታገዘ በደል ሲፈጽም የነበረው አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ዛሬ ደግሞ ጦርነት ከፍቶ አማራን ወርሯል፤ ንጹኀንን ገድሏል፤ ሴቶችን ደፍሯል፤ ሀብት ዘርፏል፤ አውድሟል፤ አሁንም ግፎችን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡

የአማራ ሕዝብና መንግሥት ራሱን የማደራጀት ሥራ በመሥራት ጠላትን የመደምሰስ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሕዝቡ በመደራጀት ባደረጋቸው አውደ ውጊያዎች ጀብዱዎች መፈጸማቸውን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ጠላትን ከክልሉ ጠራርጎ ለማስወጣት አሁንም ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ነው ያመላከቱት፡፡

የጠላት ቡድን አሁንም በአማራ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ በደሎችን ለማድረስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ጠላት ከቻለ አማራን አጥፍቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማው አድርጎ እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ የአማራ ሕዝብ በመደራጀትና በአንድነት በመንቀሳቀስ ጠላትን መቅበር ይገባዋልም ብለዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ነጻነቱንና ፍትሕን ማግኘት የሚችለው በክንዱና በመስዋእትነት ነው፤ ይህም ተደራጅቶ በመውጣትና በመታገል ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ሁሉም ወደ ወሎ ይትመም የሚለው የክተት ጥሪ በተግባር እየታየ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

እድሜና ጤና የሚፈቅድላቸው የክልሉ ነዋሪዎችም ወደ ወሎና ወደ ሌሎች ግንባሮች እንዲዘምቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቀረበው ጥሪ መሠረት ወደግንባር በመጉረፍ አማራ አንድነቱን ማሳየት አለበት፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ ጠላትን እስከ መጨረሻው ለመደምሰስ መንቀሳቀስ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡

ባለሀብቶችና ምሁራን በየድርሻቸው ወረራውን ቡድን ለመቀልበስ ተልእኳቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ጠላትን ማሸነፍ ፣ ደኅንነትን ማስከበር እና ሕልውናን ማስጠበቅ የሚቻለው በአንድነት ስንነሳ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ÷ ደጀን መሆን የሚገባው ደጀን በመሆን፣ መዝመት የሚችል በመዝመት የጠላትን ቅስም መስበርና ዳግም ወረራ እንዳይፈጽም ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.