Fana: At a Speed of Life!

የሽብር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በጋራ መመከት ይገባል -የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች እያደረሰ ያለውን ጥፋት ተጋግዞ በጋራ መመከት እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ አስታወቀ።
መጅሊሱ በኮምቦልቻ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች 10 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የድጋፉ አስተባባሪ ሸህ መሃመድ ዛኪር እንደገለጹት፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ዘግናኝ ድርጊት ፈጽሟል።
ወራሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች ሁለንተናዊ ጥፋት መፈጸሙን እንደቀጠለም ተናግረዋል፡፡
“በእዚህ የጥፋት ተግባር በሰውና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የጋራ በመሆኑ ተጋግዘንና ተደጋግፈን ችግሩን መመከትና ማለፍ ይገባናል” ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ የሰበታ፣ ቡራዩ፣ ዱካምና ሱሉልታ ከተሞችን እንዲሁም አል ኢህሳን በጎ አድራጎት ማህብርንና ሌሎች አካላትን በማስተባበር 10 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ሸህ መሃመድ ተናግረዋል።
በድጋፉ ዱቄት፣ ሩዝ፣ ማኮሮኒ፣ ዘይት፣ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁስና የተለያዩ አልባሳት ለተፈናቃዮች መለገሳቸውን ተናግረዋል።
“የገጠመው ሀገራዊ ፈተና በድል እስኪያልፍ ድረስ መጅሊሱ ህብረተሰቡን በማስተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም አክለዋል።
የመጅሊሱን ድጋፍ የተረከቡት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘሪቱ ሁሴን በበኩላቸው፥ የጥፋት ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ዘግናኝ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።
“በተለይ በሴቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው በደል ታሪክ ይቅር አይለውም” ያሉት ኃላፊዋ የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍና ከጎናቸው መሆን ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ መንግስት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ እየሰራ ቢሆንም ከተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ ነው።
“የኦሮሚያ ክልል መጅሊስ ያደረገው ድጋፍ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል ያግዛል፤ ለተደረገው ድጋፍም እናመሰግናለን” ብለዋል።
አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ወይዘሮ ዘሪቱ ጠይቀዋል፡፡
ከደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፥ በጥፋት ቡድኑ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በኮምቦልቻና ደሴ አካባቢ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ700 ሺህ አልፏል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.