Fana: At a Speed of Life!

33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

የዘንድሮው የጉባኤው መሪ ቃል “ግጭትና ጦርነትን በማስቆም ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት” የሚል ነው።

በአጠቃላይ በጉባዔው ላይ ከ30 የሚበልጡ የአፍሪካ ሀገራት ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የሰባት ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የሀገራት ምክትል ፕሬዚዳንቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በመክፈቻው ላይ ላለፈው አንድ ዓመት የህብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የነበረችው ግብፅ ለባለተራዋ ደቡብ አፍሪካ ስፍራውን አስረክባለች።

ይህንንም ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጉባኤውን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት በጉዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ 2019 በሰላምና ፀጥታ ረገድ የተሻለ አፈጻጸም መታየቱን ገልፀው፤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ግን አሁንም በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።

ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህመት አክለውም፥ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም እቅድ ማንንም ሳያማክር በተናጠል የቀረበ በመሆኑ ህብረቱ እንደማይቀበለው ገልፀዋል።

ኮሚሽንሩ እቅዱ የመንግስታቱን ድርጅት ህግ የጣሰ እና በአፍሪካ ህብረት ተቀባይነት የሌለው ብለዋል።

ቻይና ባጋጠማት የኮሮና ቫይረስ ችግር ህብረቱ ከጎኗ መሆኑንም ኮሚሽነሩ በንግግራቸው አክለው አንስተዋል።

ኮሚሽንሩ አዲሱን የ2020 የህብረቱን ሊቀ መንበር የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን የሰላም ኖቤል ሽልማት ተሸላሚ በመሆናቸው እንካን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

33ኛ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በቆይታው ከመሪ ቃሉ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

በተጨማሪም የአጀንዳ 2063 አፈፃፀም የሚገኝበትን ደረጃ በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀውን አህጉራዊ ሪፖርት መሪዎቹ የሚገመግሙ ይሆናል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የተመድ ዋና ፀሃፊን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ድርጅቶች ሀላፊዎች እና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።

ተስፋዬ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.