Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች አሰቃቂ ወንጀሎች መፈጸሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎች እና ሰብዓዊ ሕግጋትን በመጣስ በሰላማዊ ዜጎች አሰቃቂ ወንጀሎች መፈጸሙን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተጠቀሱት አካባቢዎች የተፈጸመውን ወንጀል ምርመራን እና የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት ውጤቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ወንጀሎቹ በአማራ ክልል በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች የተፈጸመ ሲሆን፥ ምርመራው የተካሄደው አካባቢዎቹ በአሸባሪው ህወሓት ተይዘው በነበሩ እና ኋላ ላይ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ነጻ በወጡ አካባቢዎች ላይ ነው ብሏል።

ወንጀሉ በደቡብ ጎንደር ዞን የላይ ጋይንት ወረዳ፣ የንፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር፣ የጉና በጌምድር ወረዳ፣ የፋርጣ ወረዳ፣ እስቴ ወረዳ /በከፊል/፣ ደብረታቦር ከተማ አስተዳደር /በከፊል/፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ በዳባት፣ ደባርቅ እና ዛሪማ ንዑስ ወረዳዎች እንዲሁም በአፋር ክልል ጋሊኮማ ቀበሌ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እና በፈንቲረሱ ዞን ሥር በሚገኙ እዋ፣ አውራ እና ጉሊና ወረዳዎች ላይ ባልታጠቁ እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ መሆኑንም ገልጿል።

አሸባሪው ቡድን በሰሜን ጎንደር ዞን በዝርዝር ማስረጃ የተለዩ የ96 ሰዎች ሞት፣ 53 የአካል ጉዳት፣ 29 አስገድዶ መደፈር፣ 11 ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ፣ 6 እገታ እንዲሁም የመንግስት፣ የግል እና የሀይማኖት የተለያዩ ተቋማት ንብረቶች ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውደመት መፈጸሙ ተረጋግጧል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች ደግሞ በድምሩ የ129 ሰዎች ሞት፣ የ54 ሰዎች የአካል ጉዳት፣ በንፋስ መውጫ ከተማ ብቻ የ73 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲሁም በርካታ ግለሰቦች ንብረት ላይ ውድመት ደርሷል፡፡

በአፋር ክልል ነሃሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋሊኮማ ቀበሌ መጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የ240 ሰዎች ሞት፣ 42 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በቀሪዎቹ ሶስት ወረዳዎች ደግሞ የ17 ሰዎች ሞት እና ለ17 ሰዎች የአካል ጉዳት እንዲሁም 7 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንደተፈጸመባቸው ተረጋግጧል፡፡

 

አንድን ሴት እስከ 15 በመሆን እየተፈራረቁ መድፈር፣ እናት እና ልጅን በአንድ ላይ መድፈር፣ ከተፈጥሮ ተቃራኒ የወሲብ ጥቃቶችን መፈፀም፣ ልጆችን በእናቶቻቸው ፊት መድፈር፤ ከደፈሩ በኋላ በጠመንጃ አፈሙዝ ብልቷን በመውጋት የፌስቱላ ተጠቂ እንድትሆን ማድረግ፣ የ8 ወር መጫትን ጨቅላ ልጇን በፈላ ውሃ ውስጥ እንጨምራለን በማለት እናትዋን በማስፈራራት መድፈር ይገኝበታል፡፡

እንዲሁም አንዲት የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ሴትን ለሶስት አስገድዶ መድፈር፣ የመደፈር ወንጀል የደረሰባቸው ሴቶች ለአባላዘር እና ለአእምሮ ጤና መታወክ በሽታዎች ተጋላጭ ማድረግ፣ የተለየ የስነ ልቦና ጫና ለማድረስ በሚል የማህበረሰቡ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶች የሆኑትን የካህናት ሚስቶችን እና ቆራቢ መነኮሳትን ለይቶ አስገድዶ መድፈር፣ በአፋር ክልል ሴቶችን ለረዥም ጊዜ አግቶ በማቆየት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በተደጋጋሚ በመፈጸም እና የህክምና እርዳታም ሳያገኙ አቆይተው መልቀቀ ናቸው።

በተጨማሪም ደባርቅ ወረዳ አብርሃም ቀበሌ ሟች ዘለቀ አስመራ የተባለ አባትን ከህጻን ልጁ ፊት አንገቱን በማረድ ሶስት ልጆቹ እግሩን እና እጁን እዲይዙ በማድረግ ከአንገቱ እስከ ሆዱ በልጆቹ ፊት በሳንጃ አካሉን መሰንጠቅ፣ የማህበረሰቡ መኖሪያ ቤቶችን የሞቱ የሽብር ቡድኑ አባላትን ለመቅበሪያነት እና ለመጸዳጃ ቤት ለምግብ ማብሰያነት መጠቀም፣ እንዲሁም ቤቶችን በማፍረስ፣ ሰዎችን በማገት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም።

በመንግስት የጤና ተቋማትን መዝረፍ እና ሙሉ በሙሉ በማውድም ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ በወንጀሉ የአስገድዶ መድፈር እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግ፣ ማህበራዊ አገልገሎት የሚሰጡ ባንኮችን፣የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ፣ የመብራት ኃይል አውታሮች ላይ ዘረፋ እና ጉዳት ማድረስ።

በአፋር ክልል የስድስት ወር ህጻን የእናቱን ጡት እንደያዘ በከባድ መሳሪያ ከእነ እናቱ ተመትቶ ተገድሏል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.