Fana: At a Speed of Life!

ባለድርሻ አካላት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት የቁጥጥር ስራን እናጠናክራለን አሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመግታት የቁጥጥሩን ስራ እንደሚያጠናክሩ ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።

የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮንትሮባንድን መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ በሐረር ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የሐረር ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር አብርሃም ሞላ እንደተናገሩት፥ በተለይ ኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችን ተከታትሎ ከመያዝ አንጻር ክፍተት ይታያል።

ክፍተቱን ለመሙላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የቁጥጥሩን ስራውን እንደሚያጠናክሩም አስታውቀዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ናስር አህመድ ፤ በዞኑ የኮንትሮባንድ እንቅሰቃሴን ለመግታት ፖሊስ እና የልዩ ሃይል አባላት ውጤታማ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ፣ መድሃኒት እና የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እያካሄዱት ያለው የቁጥጥር ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥል ብለዋል።

የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምመላሽ ተሾመ በበኩላቸው፤ባለፉት ሶስት ወራት ከ147 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አልባሳት፣ ሲጋራ፣ ኮስሞቲክስ፣ መድሃኒት፣ የተሽከርካሪ ጎማዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና ምግብ ነክ ምርቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የፌዴራል ፖሊስ፣የሐረሪ ክልል፣የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.