Fana: At a Speed of Life!

የአማራና ቅማንት ህዝቦች የሠላም ምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራና ቅማንት ህዝቦች የሠላም ምክክር መድረክ በአይከል ከተማ እየተካሄደ ነው።
 
በሠላም ምክክር መድረኩ ከሶስቱ የጎንደር ዞኖች የተሰባሰቡ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የመከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ሃይል አባላት፣ የአካባቢው የጸጥታ አካላትና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
 
የአይከል ከተማ ተወካይ ከንቲባ አቶ ለገሰ ብርቄ እንደገለጹት÷ በአሁኑ ሰአት በአካባቢው የሚታየው የሰላም እጦት፣የሰዎች እገታና ዘረፋ መሠረቱ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና የሰዎች ዝውውር ነው፡፡
 
ይህ ድርጊትም በአሸባሪው ህወሓትና በቅማንት ጽንፈኛ ቡድን ሴራ ለዓመታት ሲተገበር መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
 
የቅማንት ብሔረሰብ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበራ አለማየሁ በበኩላቸው÷የተጋረጠብን ችግር ስር የሰደደው ከውስጣችን በተገኙ ጥቅመኛ ሰዎች አማካኝነት ነው፤ እነዚህን የጥፋት መልዕክተኞችም በጋራ ተባብረን ልናስወግዳቸው ይገባል ነው ያሉት።
 
የጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው በጎ አድራጎት ማህበር አባልና በዕለቱ መወያያ ፅሁፍ አቅራቢው እጩ ዶ/ር ያሬድ ደበበ እንዳሉት÷ የዜጎች ሰላም መደፍረስና የሀገር ህልውና አደጋ ላይ የወደቀው አሁን ሳይሆን አሸባሪው ህወሓት ከተመሰረተ ጀምሮ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
አሁን ላይም አሸባሪ ቡድኑ በጥቅም የሚገዙ የአማራና ቅማንት ሰዎችን አሰማርቶ የጥፋት ስራውን ቀጥሎበታል ብለዋል።
 
በግጭት ውስጥ የሚያተርፉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ያነሱት ሰዎች አሉ ያሉት እጩ ዶ/ር ያሬድ÷በአማራና ቅማንት ህዝቦች መካከል የሚፈጥረውን ግጭት ለማስቀጠልም በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ቆይቷል ብለዋል።
 
በአንድ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች ሰላማቸውን ማረጋገጥ ይገባል፤ የሁለቱ ብሔሮች ህዝቦችም ይህንን በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ነው ያሉት።
 
በሰነድ የተደራጀ የህግ ስርዓት ባልነበረበት ዘመን “በህግ አምላክ” እያለ ሰላምን ሲያጎለብት የኖረ ህዝብ ዛሬ ህግና ስርዓት ተዘጋጅቶ ጥፋተኞችን ለህግ አሳልፋችሁ ስጡ ሲባል ዝም ማለት የለበትም ሲሉም ተናግረዋል።
አባቶቻችን ዋጋ ከፍለው ያወረሱንን ሀገር ከነክብሯ ለልጆቻችን ማስረከብ አለብን ያሉት እጩ ዶ/ር ያሬድ÷ወደፊት ልማትና እድገትን የሚያመጡ አማራጮችን በመለየትም በጋራ መበልፀግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
 
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ደግሞ የቀደመ አብሮነታችንና አንድነታችንን በመመለስ ሰላማችንን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።
 
በመካከላችን ሆነው እርስ በርስ እያጋጩና ሰላማችንን እያሳጡ የሚገኙ የህወሓት ተላላኪዎችን በመለየት ለህግ አሳልፈን እንሰጣለን ሲሉም ተናግረዋል።
 
 
በሙሉጌታ ደሴ
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.