Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለዓለም ማህበረሰብ ተደራሽ የሚሆኑ የመረጃ አማራጮቿን ማስፋት አለባት- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከመርህ ያፈነገጠውን የምዕራባዊያን ሚዲያ ዘገባ ለመመከት እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ተደራሽ የምታደርግባቸውን አማራጮች ማስፋት እንዳለባት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ምሁራን አመለከቱ::
 
ምሁራኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሀገሪቱ የተያያዘችውን አዲስ ምዕራፍ ለዓለም ህብረተሰብ በማሳየት ምዕራባውያን እያሰራጩት ያለውን የተዘባ ዘገባ መመከት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
 
ሀገሪቱ ትክክለኛ ገጽታዋንና እውነቷን በመደበኛው ብሎም በማህበራዊ የተስስር ገፆችና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በማስተላለፍ ተደራሽነቷን ማስፋት እንደሚገባት ተናግረዋል።
 
በዚህም በአሸባሪው የህውሃት ቡድን መረጃ ተቀብለው ወገናዊነት የሚታይባቸው የሚዲያ ተቋማት ለማጋለጥ እንደሚያስችል ምሁራኑ ይገልጻሉ።
 
የዩኒቨርሲቲው የልማት ጥናትና ጋዜጠኝነት መምህር ዶክተር መልሰው ደጀኔ÷ የመጀመሪያው የጋዜጠኝነት መርህ ሚዛናዊነትና ሐቀኝነት መሆኑን ያነሳሉ።
 
ይህ ደግሞ ከሁለቱ ወገኖች በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚሰበሰብ እንደመሆኑ ከአንድ ወገን ብቻ ሰምቶ ፍረጃ መስጠት ወገንተኝነት በግልጽ ያሳያል ነው ያሉት።
 
የምዕራባውያን ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ዘመቻ ከመሠረታዊ የሚዲያ ዘገባ መርህ ያፈነገጠ የአንድ ወገን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ፕሮፖጋንዳ መሆኑን አብራርተዋል።
 
የጋዜጠኝነት እሴት፣የነጻነትና እኩልነት አባት ነን የሚሉትና የሊበራል ርዕዮትን የወለዱ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚያዛቡት የሙያ እጥረት ኖሮባቸው ሳይሆን ያልተገባ ጫና ለመፍጠር ባላቸው ፍላጎት እንደሆነ አስረድተዋል።
 
”የምዕራቡ ዓለም እያደረገ ያለውን ተጽዕኖ ለመከላከል መፍትሄው እውነታውን ማሳየት ነው” ያሉት ምሁሩ÷ በተለይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚሳተፉባቸው እንደ ትዊተር የመሰሉ ማህበራዊ ይትስስር ገፆች ላይ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተደራሽ በሚሆኑ ቋንቋዎች ዜናና ሌሎች ፕሮግራሞች ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።
 
ይህም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተደራሽ በሚሆኑ አማራጮች ማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
 
አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ አንዳንድ የምዕራባውያን ሚዲያ ዘገባ ከእውነታ ያፈነገና የጋዜጠኝነት መርህ ያልተከተለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሃላፊ መምህርት ሕይወት ሃይሉ ናቸው።
 
መንግሥት አሸባሪው ቡድን እያደረገ ያለውን ጥቃት ለመከላከል የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተገቢ ባልሆነ መልኩ በማቅረብ አድሏዊነት እንደሚታይባቸው አስረድተዋል።
 
ይህም ወገንተኝነት ላይ የተኮረ ዘገባ የአሸባሪው ቡድን ሀገር የመበተን ዓላማ ያላቸውን ድጋፍ በግልጽ የሚያሳይ፣ የተጠመዘዘና ጦርነቱ ባጠረ ጊዜ እንዳይቋጭ ለማድረግ ያለመ ነው ይላሉ መምህርት ሕይወት።
 
ለዘመናት የጋዜጠኝነት መርህ ልምድና ትምህርት ሲያካፍሉ የነበሩ ምዕራባውያን ሚዲያዎች ከመርህ በማፈንገጥ ጫና ለመፍጠር መሰለፋቸው ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።
 
የኢትዮጵያ አንድነት ስሜት እየለመለመ መምጣት ለምዕባውያን ስጋት ፈጥሯል፤ ሚዲያዎቻችንም አንድነታችንን ሊያሳዩና ሊያጎሉ በሚችሉ ዘገባዎች ላይ ማተኮር አለባቸው ነው ያሉት።
 
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲክስ እየተጫወተች ያለው ሚና የማያስደስታቸው የምዕራባውያን ተፅዕኖ ለመመከት በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለመጠቀም ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
 
ምሁራኑ በተለይም የዲጂታል ዲፕሎማሲው ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራበት መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
 
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
 
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.