Fana: At a Speed of Life!

መላው የኦሮሚያ ክልል ህዝቦች እና አመራሩ ሀገርን ለማዳን ለሚደረገዉ ፍልሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲንቀሳሱ መወሰኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሽብርተኛዉ የወያኔ ጁንታ ከተፈጠረበት ቅጽበት ጀምሮ በሴራ፣ በተንኮል፣ በመግደል፣ በመዝረፍ፣ በመጥለፍ፣ … ወዘተ እድሜውን ሙሉ የኖረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ይህን እኩይ ቡድን ከነ እኩይ ግብሩ እና ከነ መርዛም አስተሳሰቡ ማጥፋት ሌላ አማራጭ የሌለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡

የሀገር ነቀርሳ የሆነው ጁንታ በህዝባችን እና በታላቋ ሀገራችን ላይ ከሩብ ክፍለዘመን በላይ ያደረሰውን መከራ፣ ስቃይ፣ እንግልት፣ ንቀት፣ እስር፣ እልቂት፣ ውድመት እና ስደት እንረሳው ዘንድ በፍጹም አንችልም፡፡

የኦሮሞን ቀሬ/ቄሮ እና የሌሎች የሀገራችንን ህዝቦች ከጫፍ ጫፍ አነቃንቆ፣ የገነፈለ በደል እና የማያቋርጥ መገደል አጥለቅልቆን የእንቢ ባይ ህዝቦች ጩኸት እና ቁጣ ምድሪቱን አስጨንቆ በደም ያመጣነውን ነጻነት በደም ጠብቀን ወደ ከፍታችን ከመጓዝ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለን በጽኑ እናምናለን፡፡

ስጋ ተቆርሶ- ደም ፈሶ- አጥንት ተከስክሶ የመጣን ህዝባዊ ለውጥ በቧልት- በእብሪት እና በንቀት ለመጣ ሀይል አሳልፎ የሚሰጥ ማንነት፣ ታሪክ እና ስነልቦና የለንም፡፡ ዳግም ባርነትን ለ መሸከም የተዘጋጀ ጫንቃ ፈጽሞ የለንም፡፡ ለውጡን ያመጣው ህዝብ ነውና- የሚጠብቀውም ህዝብ ነው፡፡

ከለውጥ በኋላም ቢሆን ለይቅርታ የተዘረጉ እጆችን ትቶ- በእብሪት እና ትምክህቱ ጸንቶ- እኩልነትን በመጸየፍ የበላይነትን ብቻ ሽቶ የሀገር ክንድ በሆነው መከላከያችን ላይ የፈጸመውን ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ እና በወገን ላይ ያመጣውን መዘዘኛ ዳፋ የኦሮሞ ህዝብ እና የክልላችን መንግስት ሁሌም በቁጭት ያስታውሱታል፡፡

ውጊያችን ከጁንታው ጋር ብቻ ሳይሆን በዚህ እኩይ ቡድን ኢትዮጵያን የማጥፋት እኩይ ፍላጎት ውስጥ ከተሰገሰጉ የውጭ እና የውስጥ የጥፋት አበጋዞች ጋርም ጭምር እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

በመሆኑም ትግላችን ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም የመጨረሻዋን ድል የምንቀዳጀዉ እኛ መሆናችንን ግን በፍጹም አንጠራጠርም፡፡ በዘመን መስመር ላይ በፍጹም ፍጥነት ጁንታው ያጠፋቸውን ብዙ ነገሮች በብዙ ትጋት- ቁርጠኝነት- ፍጥነት- መሰጠት እና አንድነት ለማስተካከል የሚደረገው ትግል የራሱን ተፈጥሯዊ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡

ይህም ሆኖ ግን አሸባሪው ጁንታ የከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራም ሆነ ሌሎች እኩይ ፕሮጄክቶቹ በህዝባችን አይተኬ ሚና እና ለዚህ በጀገኑ የሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች ርብርብ ሁሉም በድል ይጠናቀቃል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ እና መላ የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች- ሀገር እየመራ፣ መድፍ እና ታንክ እያጓራ፣ ዶላር እና ብር ለሞት ነጋዴዎች እየዘራ… እኔ ብቻ ልምራ ይል የነበረን አፍራሽ ሀይል ባዶ እጃቸውን በወኔ፣ በቁርጠኝነት እና ልብ ላይ በሚንቀለቀል የአልንበረከክም ባይነት መንፈስ ተዋግተው ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥረውት ሲያበቁ፣ እንደ እባብ አፈር ልሼ ልነሳና ልንደፋቸው ብሎ የሚንፈራፈርን መርዛማ ቡድን አናቱን ቀጥቅጦ እንዳያንሰራራ የመቅበር ጉልበት እና ህዝባዊ አንድነት በፍጹም አይገዳቸውም፡፡

ትላንትና ከኋላው የተወጋውና ታሪክ ሊረሳው የማይችል መራራ የበደል ሀሞት የተጋተው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በጀመረው አዲስ የመቻል ተጋድሎው እና መቼም በማንም ሊቆም በማይችለው ሀገርን የማሻገር ሩቅ ጉዞው ይህንን የጥፋት ቡድን አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣው እሙን ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ ጀግናዉ የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ሌሎች የጸጥታ አካላት እና ደጀን የሆነዉ የሀገራችን ህዝብ ሀገርን ከአሸባሪዉ የጁንታ ቡድን ለመጠበቅ እያደረጉ ላሉት ተጋድሎና እየከፈሉት ላለዉ ወድ መስዋዕትነት ያለንን ልባዊ አክብሮት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የምንዋጋው የኦሮሞ እና የመላ ኢትዮጵያውያንም ታሪካዊ ጠላት ከሆኑ እኩይ ሀይሎች ጋር ነው፡፡ በመንግስት እና በእኩይ ሀይሎች መሀከል ያለው የትግል መልክ በሁሉም ፈርጆች አቻ ውጊያ ለማድረግ የማይመች ዝንቅ መልክ አለው፡፡

ይኸውም ጁንታው ተላላኪዎቹ የሚዋጉት ውጊያ የህዝብን ደህንነት፣ የመሰረተልማቶችን ሁነት፣ የከተሞችን ህይወት፣ የአለምአቀፍ ተቋማትን የጦርነት አካባቢዎች የማገልገል ነጻነት… ወዘተ ከግምት ያስገባ እና ለነዚህም ጉዳዮች የሚጨነቅ አይደለም፡፡ ይህም የውጊያውን መልክ በብዙም ይለውጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት እነዚህን መሰረታውያን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና በሀላፊነት መንፈስም ነገሮችን መርምሮ ጦርነቱን በመምራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም አጠናቆ ወደ ልማታችን ለመዞር በሚያደርጉት ትግል ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ እና የክልላችን መንግስት ከፊት ሆነው እንደሚጋፈጡ እና የድል ሪቫንም እንደሚቆርጡ ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡

የጠላቶቻችን አሰላለፍ እና የጠላትነት ጽንፍ ከውጭ እስከ ውስጥ የተዘረጋ እና በክልላችን ውስጥም በእነርሱ ደረት በጁንታው ሳንባ የሚተነፍሱ ሽብረተኛ ቡድኖችን ለማጽዳት የጀመርነው ትግል ቀላል ባለመሆኑ ይህንንም አጠናክረን በመቀጠል ጠላቶቻችን ያሉበት ሆነው ኦሮሚያን በተላላኪ የውስጥ ባንዳ አመቻችነት የጦርነት አውድማ የማድረግ ስር የሰደደ ህልማቸውን በአጭር ጊዜ ወደ ቅዠትነት እንቀይረዋለን፡፡

በመሆኑም የጀመርነው ትግል መልኩ ብዙ ግን ደግሞ ግቡ አንድ በመሆኑ የክልላችን ልዩ ሀይል፣ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮቻችንም በደም ያመጣነውን ነጻነት መልሶ ሊነጥቀን ከሚንፈራገጠው ጁንታ ለመጠበቅ እና ለማዝለቅ ከህዝብ እና መንግስታቸው ጎን በመቆም እንደወትሮው ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

የክልላችንም ህዝብ በጦርነቱ ባህርይ እና በጠላቶቻችን አሰላለፍ ምክንያት ወደፊት እና ወደኋላ፤ ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ የሚሉ የአውደ ውጊያ አዝማሚያዎች ሲኖሩ በማህበራዊ ሚድያ እና በስማ በለው ከሚነዙ አሉባልታዎች ራሱን በመጠበቅ ወደ ድል ለሚደረገው ጉዞ እንደሁልጊዜው ሁሉ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

መላ የክልላችን አመራሮችም ይህንን ህዝባዊ ትግል በትጋት በመምራት ነገ ለምንደርስበት ድል አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ ተላልፏል፡፡ ቄሮ እና ቀሬዎች እንዲሁም መላዉ የክልላችን ህዝብ በሙሉ አካባቢያቹን በንቃት እንድትጠብቁ እና ከጸጥታ አካላት ጋርም በቅርበት እንድትሰሩ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የሀይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሀደሲቄዎች እና የሀገር ሽማግሌዎችም ህዝባችንን ለሌላ ዙር ባርነት እያጨው ያለውን ይህንን የሀገር ጠላት ለመደምሰስ በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ህዝቡን በማንቃት፣ በመከታተል፣ ውስጣዊ አንድነትን በመገንባት እና ድል ስለሚያጅበው ሰላማችን በመስራት የማይተካ ሚናችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡

በመጨረሻም መላው የክልላችን ህዝቦች የከሀዲውን ጁንታ ግብአተ መሬት ለመፈጸም በአንድነት እንዲንቀሳቀሱ፣ በየደረጃዉ ያለዉ አመራርም የክልሉን ጸጥታ አካላት እና ምልዓተ ህዝቡን በመስተባበር ለማይቀረው ድል ያለንን ሁሉ ምንም ሳናስቀር በማዋል ሀገርን ለማዳን ለሚደረገዉ ፍልሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ የክልሉ መንግስት ወስኗል፡፡

ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትቀጥላለች!

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.