Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪውን ቡድን ደምስሶ ወደ ልማት ለመመለስ የጋምቤላ ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የልማት ፀር የሆነውን የጁንታውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ፊታችንን ወደ ልማት ተግባሮቻችን ለመመለስ የክልሉ ሕዝቦች ከሀገር መከላከያ ጎን እንዲቆሙ የጋምቤላ ክልል መንግስት ጥሪ አቀረበ፡፡

የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የህወሓት ጁንታ ቡድን የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከ20 ዓመታት በላይ ሲጠብቀውና በችግሩ ጊዜ ከጎኑ በማይለየው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሃይላችን ላይ ታሪክ የማይረሳው ክህደት ከፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያውያን ላይ ሁሉንም አይነት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡

ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥፋት አስቦና አቅዶ የተነሳን ሀይል ማሸነፍ የሚቻለው እንደ ህዝብ አንድ ሆኖ በመቆምና በመመከት ብቻ እንደሆነ በጽኑ እናምናለን፡፡ ጠላት ከመሳሪያው በላይ በሚለቃቸው ፕሮፓጋንዳዎች ካሸበረን አንድ ሆነን መቆም ስለማንችል ህልውናችንን ለማስቀጠል እንቅፋት ይፈጥራል፡፡

በመሆኑም ጠላት በግንባር እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለማካካስና የጦሩን ስነ ልቦና ለመገንባት እንዲሁም ለወገን ጦር ደጀን የሆነውን ህዝብ ለማደናገር የሚጠቀምበት የውሸት ታክቲክ መሆኑን በውል በመረዳት ወቅቱን የሚመጥን ስነ-ልቦና መገንባት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡

ትላንትና ከኋላው የተወጋውና ታሪክ ሊረሳው የማይችል መራራ በደል የደረሰበት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በጀመረው አዲስ የማሸነፍ ተጋድሎው እና መቼም በማንም ሊቆም በማይችለው ሀገርን የማሻገር ሩቅ ጉዞው ይህንን የጥፋት ቡድን አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣው ምንም ጥርጥር የለንም፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ለይቅርታ የተዘረጉ እጆችን ትቶ- በእብሪት እና ትምክህቱ ጸንቶ- እኩልነትን በመጸየፍ የበላይነትን ብቻ በመፈለግ የሀገር ክንድ በሆነው መከላከያችን ላይ የፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት የጋምቤላ ህዝብ እና የክልላችን መንግስት ሁሌም በቁጭት ያስታውሱታል፡፡

ውጊያችን ከጁንታው ጋር ብቻ ሳይሆን በዚህ እኩይ ቡድን ኢትዮጵያን የማጥፋት እኩይ ፍላጎት ውስጥ ከተሰገሰጉ የውጭ እና የውስጥ የጥፋት ሀይሎች ጋርም ጭምር እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

በመሆኑም ወገናችን የሆንከው የትግራይ ህዝብ ከሠላም ወዳዱ ህዝባችን ጎን በመቆም በልጆችህ ህይወት ቁማር የሚጫወት እና ለአንድነታችን፣ ለሠላም፣ ሉዓላዊነት ነቀርሳ የሆነውን ይህን የጥፋት ቡድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ርብርብ ከጎናችን እንድትሆኑ ወንድማዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

በሌላ በኩል የልማታችን ፀር የሆነውን የጁንታውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ደምስሰን ፊታችንን ወደ የልማት ተግባሮቻችን ለመመለስ የክልላችን ሕዝቦች ከሀገር መከላከያ ጎን እንዲቆም የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

የክልላችን መንግስትና መላው የክልላችን ነዋሪዎች በማስተባበር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በሰው ኃይል፣ በአይነት፣ በገንዘብና በሞራል እየደገፈ የቆየ ቢሆንም ካለው ወቅታዊ አሳሳቢ የህልውና ጉዳይ ይህንን የህዝባችን ጠላት የሆነውን የጥፋት ቡድን ግብዓተ- መሬቱን ለማፋጠን የጀመርነውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የገጠሟትን የህልውና አደጋዎች በሙሉ የቀለበሰችው በህዝቦቿ ጠንካራ አንድነትና የተባበረ ክንድ ነው። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ካልዘረፍኳትና እንደወትሮው ረግጬ ካልገዛኋት ትፍረስ በሚል ስግብግብ ፍላጎት ክህደት የፈጸመብንና ጦርነት የከፈተብንን የህወሃትን ወራሪ ጁንታ የምንሰብረውና የምንቀብረውም ከታሪካችን በወረስነው በዚሁ የጀግንነትና የአንድነት መንፈስ ብቻ ነው፡፡

በመሆኑም ትግላችን ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም የመጨረሻዋን ድል የምንቀዳጀዉ እኛ መሆናችንን ግን በፍጹም አንጠራጠርም፡፡ በዘመን መስመር ላይ በፍጹም ፍጥነት ጁንታው ያጠፋቸውን ብዙ ነገሮች በብዙ ትጋት- ቁርጠኝነት- ፍጥነት- መሰጠት እና አንድነት ለማስተካከል የሚደረገው ትግል የራሱን ተፈጥሯዊ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡
የክልላችን ፀጥታ አካላትና ወጣቶች ክልላችን ጋምቤላ ድንበር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በውስጥ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር፣ የሸኔ ታጣቂዎችና የጁንታውን ዓላማ የሚያራግቡ ጥቂት ፀረ-ሠላም ኃይሎች የሚንሳቀሱበት በመሆኑ በውጪ የዘመናት ታሪካዊ ጠላቶቻችን በቅርበት የሚገኙበት በመሆኑ በንቃት አካባቢያችንን እንድትጠብቁ እና የጀመርነውን ሁሉን አቀፍ የልማት እንቅስቃሴ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ሰላም ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡን ፀጥታና ደህንነት በመጠበቅ ሃገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ የክልሉ መንግስት ያሳስባል፡፡

ይህም ሆኖ ግን አሸባሪው ጁንታ የከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራም ሆነ ሌሎች እኩይ ፕሮጄክቶቹ በህዝባችን አይተኬ ሚና እና ለዚህ በጀገኑ የሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች ርብርብ ሁሉም በድል ይጠናቀቃል፡፡
የክልሉ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ ከህዝቡና ከሁሉም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በቁጭትና በጥድፊያ መንፈስ እንደሚሰራም በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን በአንድነት ከጥቃት ለመከላከል ያቀረቡትን ጥሪ የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት በሙሉ ልቡ የሚቀበል መሆኑን እየገለጽን ሀገርን ለማዳን የሚደረገውን ማንኛውም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ ጀግናዉ የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ሌሎች የጸጥታ አካላት እና ደጀን የሆነዉ የሀገራችን ህዝብ ሀገርን ከአሸባሪዉ የጁንታ ቡድን ለመጠበቅ እያደረጉ ላሉት ተጋድሎና እየከፈሉት ላለዉ ወድ መስዋዕትነት ያለንን ልባዊ አክብሮት እንገልፃለን፡፡

ጠላት የመጨረሻ እድሉን አሟጦ እየተጠቀመ ያለበት ሰዓት በመሆኑ የጦርነትን ባህሪ መረዳትና በሀሰት ከሚራገቡ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች ራሳችንን በመጠበቅ ሁሉም እንደ አቅሙ በህልውናው ላይ የመጣን አደጋ ለመቀልበስ ራሱን ማዘጋጀትና የመኖር ዋስትናውን በራሱ ለማረጋገጥ ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትቀጥላለች!

የጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት

ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.