Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የመዲናዋ የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሽብርተኛው የህወሃት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው የጋራ ግብረ ኃይሉ፥ ሀሰተኛ መረጃ የሚያስተላለፉ እና የሚያስተጋቡ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥብቅ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የሽብር ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በሰሜን ዕዝ ላይ ከፈፀመው ጥቃት ባለፈ ሀገር የማፍረስ ዓላማውን አጠናክሮ በመቀጠል ሀገሪቷን የእልቂት አውድማ ለማድረግ መረቡን ዘርግቶ ቢንቀሳቀስም በህዝብና በፀጥታ አካላት ትብብር ዓላማው እየከሸፈ ነው  ብሏል ግብረኃይሉ በመግለጫው ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅ አስመልክቶ የደህንነትና ጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ አውጥቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡

የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የተቋቋመው የደህንነትና የፀጥታ ግብረ ኃይል በሽብርተኛው ህወሃት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ እየወሰደ ያለውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡ የህዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብሏል፡፡

የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ በጥምረት በመስራቱ የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ችሏል፡፡ይህ የተቋቋመው ግብረ ኃይል አሸባሪው የህወሃት ቡድን አገሪቱን ወደ ግጭትና ትርምስ በመክተት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጎነጎነውን ሴራ ለማክሸፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡የኢትዮጵያ ቀንደኛና አደገኛ የሰላም ስጋት የሆነው ይህ አሸባሪ ቡድን ህዝቡን ለማሸበር እና ለማደናገር አሁንም የተዛቡና ሀሰተኛ መረጃዎች እያሰራጨ ይገኛል፡፡

የሽብር ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በሰሜን ዕዝ ላይ ከፈፀመው ጥቃት ባለፈ ሀገር የማፍረስ ዓላማውን አጠናክሮ በመቀጠል ሀገሪቷን የእልቂት አውድማ ለማድረግ መረቡን ዘርግቶ ቢንቀሳቀስም በህዝብና በፀጥታ አካላት ትብብር ዓላማው እየከሸፈ ነው፡፡

ቡድኑ ለ27 ዓመታት ሲያደርገው እንደነበር ዛሬም በህዝቦች መካከል የተለያዩ የጥላቻና የልዩነት ወሬዎችን በማናፈስ ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳ ልዩ ልዩ ሴራዎችን ሸርቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ የጥፋት ኃይሉ በተደጋጋሚ ባስተላለፈውና ደጋፊዎች ባናፈሱት የተዘባ መረጃ በአማራ እና በአፋር ክልል በርካቶችን ከቀዬቻው አፈናቅሏል በደረሰበት ቦታ ሁሉ ንፁሃንን ገድሏል፡፡

ሽብርተኛ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ መንግስት እየወሰደ ያለው ህጋዊ እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን የነቃ የህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ስለሆነ መኖሪያ ቤት ተከራይተው በጋራ የሚንቀሳቀሱ፣ ሰዋራ ስፍራ በመምረጥ ግንኙነት የሚያደርጉ የሽብር ቡድኑ ደጋፊዎችና ናፋቂዎች መኖራቸውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ መኖሪያ ቤት፣ ንግድ ቤት፣ መጋዘን እና ተሽከርካሪ ያከራያችሁ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተከራዮችን ማንነት በጥንቃቄ በማጣራት መረጃውን በአስቸኳይ ለፖሊስ እንድታሳወቁ ግብረ ኃይሉ ያሳስባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግብረ ኃይሉ ሽብርተኛው ቡድንና ደጋፊዎቹ ህብረተሰቡን ለማደናገርና የጥፋት ተልዕኮአቸውን እውን ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ የተለያዩ የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ለመንቀሳቀስ ዕቅድ እንዳላቸው የደረሰበት መሆኑን እየገለፀ ይህንን መሰል አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በአካባቢው ላለ የጸጥታና የደህንነት ተቋም በአስቸኳይ እንዲያሳውቅ ጠይቋል።

የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሽብርተኛው የህወሃት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጋራ ግብረ ኃይሉ እያስታወቀ ሀሰተኛ መረጃ የሚያስተላለፉ እና የሚያስተጋቡ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥብቅ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

ለከተማችን ሰላምና ደህንነት እየተጋ የሚገኘው የፀጥታ አካላችን በሽብርተኛው ህወሃት ደጋፊዎችና ናፋቂዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ህዝቡ ተገንዝቦ በየአካባቢው በመደራጀትና በመቀናጀት ለፀጥታ አካሉ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ወይም የፖሊስ አገልግሎትን ማግኘት ሲፈልግ በ011-1-11-01-11 ወይም በነፃ ስልክ መስመር 991፣ 997 መጠቀም እንደሚችል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.