Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በሰራዊታችን ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ታሪክ ይቅር የማይለው ነው – የሶማሌ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)የሀገር አንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው አስነዋሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ መፈፀሙ እንደማይዘነጋ የሶማሌ ክልል መንግስት ገለጸ።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደ ሲሆን ÷ የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

አሸባሪው ህውሓት በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ክንድ ከማእከላዊ ስልጣን ከተወገደበት ማግስት ጀምሮ በስልጣን ዘመኑ ሲሰብክ የኖረውን ልዩነትና ጥላቻ በማራገብና ደም አፋሳሽ ግጭቶችን በመቀስቀስ በርካታ ንፁሃን ዜጎች እንዲሞቱና እንዲፈናቀሉ ማድረጉ ይታወቃል።

ከዚህም አልፎ የሀገር አንድነትና የሉአላዊነት መገለጫ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው አስነዋሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ መፈፀሙም አይዘነጋም።

በተጨማሪም በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸምና ጦርነት በመክፈት የጅምላ ጭፍጨፋን ጨምሮ ዘግናኝ ግፍና በደል እየፈፀመ ይገኛል።

አሸባሪው የህወሓት ሀይል በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት የሶማሌ ክልል ሕዝብ በሞግዚት አስተዳደር ስር እንዲቆይና በሃገሩ ጉዳይ የዳር ተመልካች እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር ግድያና አስገድዶ መድፈርን የመሰሉ በርካታ ኢ-ሰብአዊ የጭካኔ ድርጊቶችን በሕዝባችን ላይ ሲፈፅም መኖሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በተላላኪዎች ትናንት ሲያስገድልና ሲያዘርፍ የነበረውንየሶማሌ ክልል ሕዝብ ዛሬም እድሉን ካገኘ ሌሎች ጨካኝ አሻንጉሊቶችን በመጠቀም የትናንቱን ግፍና አውቅልሃለው ባይነት ከመድገም የማይመለስ ራስ ወዳድ አደገኛ ቡድን መሆኑን ህዝባችን ይገነዘባል።

ስለሆነም ይሔ አሸባሪ ቡድን ወደ ስልጣን ለመመለስና በሕዝባችን ላይ ዳግመኛ የጭቆና ቀንበሩን ለመጫን የሚያደርገውን መፍጨርጨር ለመቀልበስ እና እስከወዲያኛው ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት እስከአሁን ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ግንባር ቀደም ሆኖ የሚሰለፍ መሆኑን ያረጋግጣል።

ይሔ አሸባሪ ሀይል የዛሬ አመት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ ጥቃት ካደረሰበት ማግስት ጀምሮ የሶማሌ ክልል ሕዝብና የክልሉ ፀጥታ ሀይል ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራት የምትዋሰንበትን ሰፊ ድንበር መከላከያ ሰራዊቱን ተክቶ ከአልሸባብ ሰርጎ ገቦች በመጠበቅ አኩሪ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።

አሁንም አሸባሪ ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን በአስተማማኝ ደረጃ መቀልበስ እንዲችልና ሀገር የማዳን ተልእኮውን በስኬት እንዲወጣ የምናደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ የውስጥ ሰላማችንን እና የሀገራችንን ድንበር የመጠበቁን ሀላፊነት አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እንገልፃለን።

ጀግናው መከላከያ ሰራዊታችንና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች በግንባር ተሰልፈው እያደረጉ ላሉት ተጋድሎና እየከፈሉት ላለዉ የህይወት መስዋዕትነት ያለንን አክብሮት በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

በመጨረሻም የክልላችን አመራሮች ፣ ኡጋዞች ፣ የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶች እና በአጠቃላይ የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች በሙሉ አሸባሪው ሀይል በሚያሰራጨው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሳትረበሹ አካባቢያችሁን በንቃት መጠበቅን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ በሆነው የትግል መድረክ በምትችሉት ሁሉ ተሳትፎ እንድታደርጉና ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ያላችሁን የደጀንነት ሚና አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን።

ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ!!
ድል ለመከላከያ ሠራዊታችን!!

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.