Fana: At a Speed of Life!

ደማችሁን የምንመልሰው ለታላቅ ህዝብ የምትመጥን ታላቅ ሀገር በመገንባት ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ)አሸባሪው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ አንደኛ አመት መታሰቢያን በማስመልከት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሌሎችን ማኖር ጀግንነት ቢሆንም ለራስ ሞቶ ሌሎችን ማኖር ግን ከጀግንነትም የሚሻገር ብጽእና ይጠይቃል፤ እናንተ ለእኛ ጀግኖችም- ብጹአንም ናችሁ፡፡

ምድር ጨለማ ለብሳ ዝም ባለችበት፣ የመአልት ፍጡራን ለሌሊት አራዊት ስፍራውን ለቀው በያሉበት ባሸለቡበት በዚያ ውድቅት ሌሊት የሆነባችሁን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እና ክህደት መቼም አንዘነጋውም፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም እንደ ሀገር፣ እንደ ህዝብ፣ እንደሰው ፍጡርም ያዘንበት- አንገት የደፋንበት- በቁጭት የተብሰከሰክንበት ጥቁር ቀን ሆኖ ቢያልፍም- የሆነውን ሁሉ ዘግናኝ እልቂት ለአፍታም ቢሆን አንረሳውም፡፡

የእናንተ ሞት- ስቃይ- ጭፍጨፋ እና እልቂት ህዝብ እና ሀገርን በማስቀደማችሁ የመጣባችሁ የጠላት መአት ነውና ሀገራችሁ እና ህዝባችሁ መቼም አይረሷችሁም፡፡

የሞታችሁለት ህዝብ እና በነፍሳችሁ ያቆማቿት ሀገር ካሰባችሁላቸው የብልጽግና ማማ ላይ በኩራት እስኪሰየሙ ድረስ እኛ ወገኖቻችሁ ፍጹም እረፍት አይኖረንም፡፡

ደማችሁን የምንመልሰው ለታላቅ ህዝብ የምትመጥን- ታላቅ ሀገር በመገንባት እና ለሀገራችሁ የነበራችሁን ሩቅ ህልም እውን በማድረግ ነውና ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የብልጽግና እና የዴሞክራሲ ጸሀይ ደምቃ እስክትወጣ ድረስ የአይኖቻችን ሽፋሽፍቶች በዝንጋኤ አይከደኑም፡፡

ሳተናዎቹ የሀገር ማገር እና ዋልታዎቻችን- መቼም አንረሳችሁም!

እዝነት እና ርህራሄ ለእንሰሳትም ጭምር በሚቸርበት ሀገር ላይ የበቀሉ እኩያን ስብስቦች በዚህ ምድር- በዚህ አፈር ላይ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ግፍ እና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ፈጽመውባችሁ በአካል ብናጣችሁም በመላ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ግን ለዘለአለም ትኖራላችሁ፡፡

እናንተን የበሏችሁ ሰው በላ አረመኔዎች የታላቋ ሀገራችሁ እና የሞታችሁለት ህዝባችሁን የብልጽግና ጀምበር ለማደብዘዝ እና በሌላ የባርነት ካቴና ለመጠፍነግ እየተንፈራገጡ ቢሆንም በኢትዮጵያ ምድር ግን ይህ አይነቱ ቅዠት መቼም ቢሆን መች በፍጹም እውን አይሆንም፡፡

ሞት ማለት ከመኖር ወዳለመኖር የመሸጋገር ተፈጥሯዊ ኡደት ቢሆንም የእናንተ ግን እንደዚህ አይደለም ፤ በፍጹም፡፡

ይልቁንም እናንተ በመውደቃችሁ መቆማችንን- በሞታችሁ ህይወታችንን- በስቃያችሁ እረፍታችንን- በመታጣችሁ ህልውናችንን አረጋግጣችሁልናልና በዘለአለም ክብር እና ከልብ በታተመ ፍቅር ሁሌም እንዘክራችኋለን፡፡

በውድቅት ሌሊት ያመናችሁት ከከዳችሁ፣ ያጎረሳችሁት ከነከሳችሁ፣ ያቀፋችሁት ከገፋችሁ፣ ያኖራችሁት ከገደላችሁ ዛሬ አንድ አመት ሆነ፡፡

በዚህ እለት እናተን ያጣንበት- የሀዘን ከል የለበስንበት- እንደ ሀገር እንባ የተራጨንበት – በቁጭት ተብሰክስከን ለድል የጀገነ እልህ የቋጠርንበት ቀን መሆኑን ብቻ ዘክረን የምናልፍበት ቀን አይደለም፡፡

ይልቁንም ይህ ቀን ለወደቃችሁለት አላማ ስኬት- ለህዝባችን ብልጽግና እና ዘላለማዊ አብሮነት- ለሀገራችን ክብር እና የማይደፈር ሉአላዊነት ያለንን ለመስጠት እንደገና የምንጀግንበት እና ቃልኪዳናችንንም የምናድስበት ታሪካዊ ቀናችን ነው፡፡

ይህንን ስናደርግ ደግሞ የያዝነው እውነት እና የእውነት ባለቤት የሆነው አምላክ ከእኛ ጋር ናቸውና አሸናፊነታችን በፍጹም አይቀሬ ነው፡፡ ፈጣሪን እና እውነትን የያዘው ህዝብ ታላቋን ሀገር ወደ ከፍታዋ ያሻግራታል፡፡

ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትቀጥላለች!
ነፍሳችሁ በሰላም ትረፍ!

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.