Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህውሃት ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እና ሌሎች ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን ፈጽሟል – የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች ሪፖርት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህውሃት ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እና የንብረት ዘረፋ ጭምር መፈፀሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በጋራ ያወጡት ሪፖርት አመለከተ፡፡
 
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ክፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተውን ግጭት አስመልክተው የደረሱበትን የጥናት ውጤት ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርገዋል፡፡
 
በዚህም የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም የጦር ካምፑን መቆጣጠራቸውን ሪፖርቱ አመላክተዋል።
 
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ አባል የሆኑና ራሳቸውን ‘’ሳምሪ’’ በሚል ስያሜ የሚጠሩት ቡድኖች በማይካድራ ከ200 በላይ አማሮችን በግፍ መግደላቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
 
ጥቅምት 30 እና ህዳር 1 ቀን 2013 ’’ ሳምሪ’’ የተባሉት ኃይሎች በማይካድራ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጅ ወንዶችን ለይተው መጨፍጨፋቸውንም ጠቁሟል፡፡
 
ቡድኑ ማይካድራ ላይ በተለይ ወጣቶችን በመለየት መግደሉን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
በድርጊቱ የአካባቢው ባለስልጣናት፣ ፖሊስ እና ሚሊሺያ ቀጥተኛ ተሳትፎና ድጋፍ እንደነበራቸውም ተገልጿል፡፡
 
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ጠዋት የአካባቢው ባለስልጣናት የአማራ ተወላጆችን በመለየት መታወቂያ በመጠየቅና ሲም ካርዳቸውን በመቀማት ተግባሩን መጀመራቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
 
የአማራ ተወላጆች በእለቱ ከተለዩ በኋላ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ በቤታቸው በራቸውን ዘግተው እንዲቀመጡና ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡
 
በመቀጠል ‘’ሳምሪ’’ የተባለው ቡድን አባላት በአካባቢው ባለስልጣናትና ሚሊሺያዎች ታጅበው ቤት ለቤት በመዞር በያዙት ጎራዴ ፣ጦር፣ መዶሻና ዱላ በመጠቀም የአማራ ተወላጆች ላይ ግድያ መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡
ለማምለጥ የሞከሩትን ደግሞ የአካባቢው ፖሊሶችና ሚሊሺያዎች ጠብቀው በጦር መሳሪያ መግደላቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።
 
ጥቃቱና ግድያው በተለይ ’’ ግንብ ሰፈር’’ እና ‘’ሰራተኛ ሰፈር’’ በሚባሉ አጎራባች አካባቢዎች በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ መፈጸሙ ተብራርቷል፡፡
 
የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ አባላት በወቅቱ በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በቁጥጥር ስር ባዋሏቸው ሰላማዊ ሰዎችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ አካላዊ ጥቃትና ሌሎች አስከፊ በደሎችን ማድረሳቸውንም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
 
ኢሰብዓዊ ድርጊቶቹ በጦር ካምፖች፣ በማጎሪያ ማዕከላት፣ በሰለባዎቹ መኖሪያ ቤት ውስጥና አድራሻቸው በማይታወቅ ስፍራዎች መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡
 
ጥቅምት 30 ቀንና ህዳር 1 ቀን የትግራይ ልዩ ሃይል የታጠቁ ቡድኖች ሁመራ ላይ በተለይ የአማራ ክልል ተወላጆችን በመለየትና እጃቸውን የኋሊት በማሰርና በመሳደብ፣ ስቃይ በተሞላበት ሁኔታ በማስቀመጥ፣ በመደብደብ፣ ለበርካታ ቀናት ምግብና ውኃ በመከልከልና በረሃብ በመቅጣት የግፍ አሟሟትና ከፍተኛ ስቃይ ማድረሳቸውንም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
 
ግጭቱ እንደተጀመረ በምዕራብ ትግራይ (ማይካድራ) የሚገኙ በተለይ የአማራ ተወላጆች በትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ታግተው መሰቃየታቸውንም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
 
ከጥቅምት 30 ቀን ጀምሮ የተያዙት የአማራ ተወላጆች ወደ ሽሬ፣ አክሱምና መቀሌ ተወስደው መታሰራቸውንና የቻሉት ሲያመልጡ በርካቶቹ መገደላቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
 
የገቡበት ያልታወቁ ዜጎች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡
 
ከጥቅምት 2013 እስከ ታህሳስ 2013 ዓ.ም ባሉት ወቅቶች በትግራይ ክልል በሺመልባ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች በትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተመላክቷል፡፡
 
የትግራይ ታጣቂ ሃይል የስደተኞቹንና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋማትን ንብረት መዝረፋቸው ተጠቅሷል፡፡
 
የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚኒሻ አባላት በምዕራብ ትግራይ (ማይካድራ) እና በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የሚገኙ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችንና መሰረተ ልማቶች በመዝረፍና በማውደም ከፍተኛ ጥፋት መፈጸማቸውን አብራርቷል፡፡
የትግራይ ልዩ ኃይል አስገድዶ መድፈርንና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሰለባዎቹን ለማሸማቀቅና ሰብዓዊ ክብራቸውን ለመግፈፍ በማሰብ መፈጸሙ ተገልጿል፡፡
 
ውጊያው እንደተጀመረ ከቤታቸው ሸሽተው ያመለጡና በተለያዩ ቦታዎች ተደብቀው የነበሩ ሴቶችና ልጃገረዶች በትግራይ ልዩ ኃይለ ተይዘው ተደፍረዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡
 
በዚህም የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ከተሞችንና ወረዳዎችን በተቆጣጠሩባቸው ጊዜያት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሚስቶችን በመለየት ማሰቃየታቸውንና መድፈራቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
 
ከነዚህ ሴቶች መካከል በርካቶቹ በጥቅምት 2013 መቀሌ ላይ ታስረው መሰቃየታቸውንም ነው ሪፖርቱ የገለጸው፡፡
 
በህይወት ተርፈው ምስክርነታቸውን ከሰጡት መካከል አንዷ ግለሰብ ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሚስቶች ሞባይል ስልክ በውስጥ ሱሪያቸው ውስጥ ደብቀው በመገኘታቸው፥ በሰይፍ ተቀልተው መገደላቸውን ለመርማሪዎቹ መናገሯ ሪፖርቱን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
 
እሷም መሰል ድርጊት ከፈጸመች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደሚገጥማት ሶስት የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት እንዳስጠነቀቋትና ራሷን እስክትስት ለሶስት እንደደፈሯት ተናግራለች፡፡
 
ከአዲ ሀገረይ በህይወት ተርፋ የወጣች የአንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሚስት የሆነች ግለሰብ እንዲሁ በጥቅምት 2013፥ ሶሰት የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ቤቷን በመበርበር እንደሚገድሏት እንደዛቱባት መስክራለች፡፡
 
ከዛም ተመልሰው በመምጣት ለሶስት እንደደፈሯት በመናገር ኤች አይቪ ሊይዘኝ ይችላል በሚል ስጋት እንዳለባትና ነገር ግን ምርመራ አለማድረጓን ተናግራለች፡፡
በወቅቱ የአማራ ሴቶች ተለይተው አንድ ቤት እንዲቀመጡ በማድረግ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት እያወጡ ይደፍሯቸው እንደነበርም ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡
 
ከነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው የአዲ አገረይ ነዋሪና ከእናቷ ጋር የተጠፋፋች የ16 አመት ታዳጊ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሰዎች ሲገደሉና ቤቶች ሲቃጠሉ በመመልከቷ ደንግጣ በማምለጥ ላይ እያለች፥ ሶስት የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት እንዳስቆሟት እና ሁለቱ ወታደሮች ሁለት እጇቿን በመያዝ አንዱ ወታደር እንደደፈራት ተናግራለች፡፡
 
በዚህም የስነ ልቦና መቃወስ እንዳጋጠማትና በተደጋጋሚ ነገሩን እያስታወሰች እንደምታለቅስ ገልጻለች።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.