Fana: At a Speed of Life!

ወያኔ – ግፍ ሞልቶ የተረፈው አረመኔ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጣን ላይ ሳለ በአገር በወገን ላይ የሚፈጽመው ግፉና መከራ ሩብ ምዕት ዓመት አልፎታል። የዚህኛው የአምናው ግና በዓይነቱ የተለየ ነው።
 
አገሩን ከጠላት፣ ህዝቡን ከጥቃት ለመጠበቅ ለ20 ዓመታት በትግራይ በረሃ፣ ዱር ገደል ሲንከራተት በኖረ፥ ካገኛት የዕለት ጉርሱ እያካፈለ የትግራይን ህዝብ ህዝቤ ብሎ፥ ከጥማቱና የጥሜቱ በታደገ እንደ ጠላት ተቆጥሮ በጎን ተወጋ፡፡
 
እንኳንስ በአገሬው በዓለም ላይ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ክህደት ተፈጸመበት። ለዚያውም አብረው በኖሩ እየተጋሩ ሲበሉ ሲጠጡ በኖሩ በከሃዲ በአገሩ ልጆች!
 
ከ20 ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲያገለግል የኖረውን፣ በጋብቻ የተቆራኘውን፣ ከሚጎርሰው ቆርሶ ያጎረሰውን ወታደር ሀገር አማን ብሎ ባረፈበት የአሸባሪው ስብስብ ከጀርባው ወጋው።
 
መቶ ዓለቃ ስንታየሁ ግዛው ተዓምር በሚያስብል መልኩ ሕይወታቸው የተረፈ የጥቃቱ ሰለባ ናቸው።
 
በወቅቱ በአዲግራት ግንባር በ ግዳጅ ላይ የነበሩት መቶ አለቃ ስንታየሁ የሆነውን በቁጭት፥ በእልህና በምሬት ያስታውሳሉ፡፡
 
ሠራዊቱ ግዳጁን ፈጽሞ ረፍት ላይ እያለ ከምሽቱ 4፡00 ገደማ መብራት ጠፋ፤ የስልክ ግንኙነትም ተቋረጠ። ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከወትሮው የተለዬ እንቅስቃሴ መታዬት ጀመረ።
 
በሠራዊቱ ላይ፤ በወገን ላይ፥ ወገን ክሕደት ይፈጸማል የሚል ሀሳብ ፈጽሞ አልነበረም፡፡ ሁኔታዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ቀጥለው ከሌሊቱ 6፡00 ገደማ ተኩስ መሰማት ጀመረ፡፡
 
ተረኛ የሠራዊት አባላት ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ ቢደረግም ከትግራይ ማህጸን የተፈጠሩ የሠራዊት አባላት የክሕደት ተግባራቸውን ፥ ሰይጣናዊ ሀሳባቸውን በወገን ላይ ማሰረፍ ያዙ፡፡
 
“ጥበቃዎችን ከምሽግ አስወጥተው ትጥቃቸውን አስፈቱ፤ በአንድ ዓላማ ለዓመታት አብረን ለአንድ ዓላማ ፥ ለአንዲት አገር ክብር የተሰለፍን የሠራዊት አባላትን ለጥቃት አሳልፈው ሰጡን” ይላሉ መቶ ዓለቃ ስንታየሁ።
 
በነጋታው ያዘጋጁትን ልዩ ኀይል አግበስብሰው የወታደሩን ካምፕ ወረሩ፣ በሠራዊቱም ላይ ተኩስ ከፈቱ፡፡
 
አካባቢውም በከሃዲዎቹ ታጣቂዎች ተሞላ፤ ከዚያም የሠራዊት አባላቱን ወደ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ወሰዷቸው፡፡
 
እሳቸውን ጨምሮ ከምክትል መቶ አለቃ እስከ ጀነራል ማዕረግ ያላቸውን የጦር መሪዎች ደግሞ አባላቱን በማስተባበር አደጋ ያደርሱብናል በሚል ስጋት በሌሊት ወደ ተንቤን በርሃ ወሰዷቸው፡፡
 
የሚበላ እና የሚጠጣ በሌለበት ረጅም የእግር ጉዞ አደረጉ፤ በዚያ ላይ ዛቻው፤ ስድቡና እና ማስፈራሪያው ቀጥሏል፡፡ ወደሚፈለገው ቦታ ሲደርሱም ሊቀበሩበት የተዘጋጀ ዶዘር እና ጉድጓድ ነበር ያገኙት፡፡ ይሁን እንጂ ተዓምራዊ በሆነ መልኩ ነገሮች በቅጽበት ተለዋወጡ።
 
“ከእኔ በላይ ጦር አዋቂና አሸናፊ የለም” ብሎ የታበየውን ገዳይ የጁንታ ቡድን የሚያርበተብት ክስተት ድንገት ተፈጠረ። መድፎች ሲያጓሩ ተሰማ፤ ቅምቡላ በቅርበት መውደቅ ጀመረ- ከወገን ደራሸ ወገን።
 
የእናት ጡት ነካሾች ቀቢጸ ተስፋም ከሰመ፤ ሠራዊቱን ለመቅበር ያዘጋጁትን ጉድጓድ እና ዶዘር ጥለው ወደ ጫካ ፈረጠጡ፡፡
 
የወገን ጦር እንደ አንበሳ እያገሳ፣ እንደ አራስ ነብር እያጉረመረመ ለተሰነዘረበት ጥቃት አጸፋ እየሰጠ ታፍነው ወደነበሩት አባላት ከተፍ አለ።
 
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችና መላው ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሆ ብለው ከጠላት ጋር ተፋለሙ። ጠላት ተፍረከረከ። አይቀጡ ቅጣትም ተቀጣ።
 
ከኢትዮጵያዊ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ዕሴት እና ማንነት ያፈነገጠው የአሸባሪውና የወራረው ቡድን ኢሰብዓዊ ድርጊት ሀገር እና ሕዝብን ለማገልገል ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት በተሰባሰቡ ጀግኖች ላይ ብቻ አላበቃም፡፡
 
የትግራይን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ፥ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባሳለፈ ማግስት ጠላት ተሰባስቦ ዳግም የጥፋት በትሩን በንጹሃን ላይ ማሳረፉን ቀጠለ።
 
ማይካድራ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ በማካሄድ የተጀመረው ዘግናኝ ግፍና ጭካኔ በጭና፣ በውርጌሳ፣ በቆቦ፣ በአጋምሳ፣ በኮምቦልቻና በጋሊኮማ አካባቢዎች ተፈጽሟል፡፡ አሸባሪው ኋይል በወረራቸው አካባቢዎች ሁሉ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሀብት ተዘርፎ ወደ ትግራይ ተጭኗል፤ እንዲወድምም ተደርጓል፡፡
 
እንስሳትን ሳይቀር በጅምላ የገደለው አረመኔ አሁንም ግፉን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
 
የሀገር መከታ የሆነው የመከላከያ ሠራዊትም ይህንን ወረራና ግፍ ለመቀልበስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በየግንባሩ እየተዋደቀ ይገኛል። አሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ክህደቱ በፈጠረበት ቁጭት እንደ ንስር እየተወረወረ ጠላትን የሚያጠቃ ትንታግ ሆኗል፡፡
 
ጥቃቱ በተፈጸመ ጊዜ በአጭር ጊዜ በዛላምበሳ ግንባር መቀሌን በቅስበታዊ የግዳጅ አፈጻጸም የተቆጣጠረው የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩት ሻለቃ አንተነህ ከፈለኝ ሠራዊቱ አሁንም በጀግንነት እየተፋለመ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡
 
ቆስለው እንኳን የማገገሚያ ጊዜ ሳያስፈልጋቸው በወኔ ከጠላት ጋር የሚፋለሙ እንቁ አናብስት መኖራቸውንም መስክረዋል፡፡
 
የአሚኮ ያነጋገራቸው የሠራዊት አባላት በሰጡት አስተያየትም፥ ሠራዊቱ በጋለ ሀገራዊ ስሜት ጠንካራ ክንዱን በጠላት ላይ ማሳረፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
 
በአገራችንና በህዝባችን ላይ ሲፈጽም የኖረውና እየፈጸመ ያለው ግፍ ሞልቶ እየፈሰሰ በመሆኑ የእጁን የሚያገኝበትና ግብዓተ መሬቱ የሚፈጸምበት ጊዘው ደርሷል ነው ያሉት ግንባር የሚገኙት የሰራዊቱ አባላት።
 
ጠላትን በተባበረ ክንድ ከማጥፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ያሉት የሠራዊቱ አባላት ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ግንባር ድረስ በመሰለፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ ኃይልና ደጀን መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
 
ካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.